ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ተንሰራፍቶ አይነቃነቄ የመሠለው የሮማ ኢምፖየር አይኗ ስር ሲፈራርስ በአርምሞ ታዝባለች።
የእነ ፔርሺያን አይነኬ ይባል የነበረ የጊዜው ሃያል ሀገራትን አካልሎ የዋጠ እናም የገዘፈ ግዛት እንክትክት ብሎ ሲወድቅ የተመለከተች ትዝታ ብዙ ነች። ኢትዮጵያ።
ከጥንት እስከ ዛሬ ስሟን አስጠብቃ ነበረች፣ አለች፣ ትኖራለች።
በሀገረ-መንግስት ግንባታ ታሪኳ ከዓለም ሀገራት አኳያ ጉምቱ ብትሰኝ የማይበዛባት ናት የሀገራት አንጋፋዋ ኢትዮጵያችን።
የዚህችን ቀልብ ሳቢና እምቅ ታሪኳ በቅጡ ያልተጠናላት ሚስጢረ-ብዙ ሀገርን ድብቅ እውነታ ለማወቅ የቋመጡ አውሮፓውያን በብዙ ስለመልፋታቸው ሀገራትንና ታሪካቸውን አሳሽ ነን ከሚሉቱ መካከል ጀምስ ብሩስን ማስታወስ በቂ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁናዊዋ ሉላዊት /Global/ዓለማችንም አስፈላጊነቷና በወሳኝ ስትራቴጂክ አቀማመጧ ዓይን የሚጣልባት መሆኗ የቀጠለ ብቻ ሳይሆን መዓት ዋጋዎችን እያስከፈላት…ወሳኝ ብሄራዊ ጥቅሞቿን እንድታጣ መደረጓም አብሰልሳይ የታሪክ እውነታዋ ነው።
እኛ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከምንም በላይ አጽንኦት ሰጥተን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ለሰከንድ የማናቅማማበት ጉዳይ ቢኖር…የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ነው።
በስኬት ተጠናቆ በቅርቡ ለምርቃት ዝግጁ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዕውን እንዲሆን በጽናት የከፈልነውን ውድ መስዋዕትነት በኩራት የምናስታውሰው ብቻ ሳይሆን የግድቡ አርማታ ሲላቆጥ ውሃ ብቻ ሳይሆን የእኛም ደም እንደነበረበት ስናስብ ታላቅ ደስታ እየተሰማን ነው።
ለህላዌዋ ስለምንሞትላት ኢትዮጲያችን ብሄራዊ ጥቅም መረጋገጥ ለአፍታ የማንዘናጋ ከመሆናችንም በላይ የህዳሴው ግድብ ድል በቀይ ባህርም ተደግሞ የተነጠቅነው እውነታችን እንደሚመለስልን በልበ – ሙሉነት እናምናለን።
ስንሞትላት በደመ – ነፍስ አይደለም።አካላችንን ስንገብርላትም እንዲሆ በተራ ጀብድ ሳይሆን ታሪኳን ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው።
በባዕድና ባንዳ እኩል ሴራ እንዴት ከቀይ ባህር ተገፍተን የበዙ ጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ወሳኝ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን እንዳጣን ነጋሪ ሳንሻ ጠንቅቀን የምናውቀው ጉዳይ ነውና የኢትዮጵያችንን ዕንባ ለማበስ ሁሌም ዝግጁ ነን።
“የቀይ ባህር የታሪክ ስብራቷ ታክሞ የታላቅ ሀገርነት እውነቷ ይመለሳል” ብለን በጽኑ ስናምንም ያለ አንዳች ጥርጥር ነው።
በአስቻለው ሌንጫ





