”የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነት እና የአንድነት ምልክት” 90ኛው ዓመት ምስረታ ቀን አከባበር መሪ ቃል ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከምስረታ አንስቶ አሁን የደረሰበት ከፍተኛ የአድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ በባለፉት ጊዜያት በርካታ ዉጣ ዉረዶችን አልፏል፡፡
አየር ኃይል በታሪክ ሂደት ዉስጥ ከአንድም ሁለት ጊዜ እንደተቋም የመፍረስ አደጋ አጋጥሞታል፡፡ መጀመሪያ በጣሊያን ወረራ በጦርነቱ ሂደት በመዉደሙ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በ1983 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ስልጣን በያዘዉ መንግስት ተቋሙን የማፍረስ እርምጃ፣ አየር ኃይልን ከነበረበት ደረጃ በማዉረድ ብዙ ዓመታት ወደ ኋላ አንዲንሸራተት አድርጎታል። ወደ ኃላ የመንሸራተቱ ጉዳት አሻራው ዛሬም ድረስ ተቋሙን ከውድቀት ለማንሳት በሚደረግ ጥረት አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።

ሆኖም አየር ኃይልን በሁሉም ረገድ በማዘመንና ሁለንተናዊ ብቃቱን በማሳደግ የመከካከያ ሰራዊታችን ጠንካራ ክንድ፣ የሉአላዊነታችን መከታና የህዝባችን ኩራት ለማድረግ ባለፉት አምስት አመታት በተሰራ ስራ በተግባር የሚለካ ዉጤት እያሳየ ነው። የተቋሙን ገናና ስም አኩሪ ታሪክ በአዲስ መልክ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለታላቅ ሀገር የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል እየተገነባ ይገኛል።
ተቋሙ ከተመሰረተበት ዓላማ ዉጭ የተለያዩ ፖለቲካዊ ስም እና ምክንያቶች እየተሰጡ ለማክበር ሲሞከር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአየር ኃይል ምስረታ ቀን አከባበር መዛባቱ ብቻ ሳይሆን ረዥም ታሪክና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለዘመናት ሲያከናዉን የነበረዉን ታላቅ ገድል በመሰረዝ ለይስሙላ ለማከበር ሲሞከር ቆይቷል።
አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባው ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ሲሆን፣ አውሮፕላኗም ፓቴዝ 25-A2 (Potez 25-A2) የተሰኘች የፈረንሣይ ስሪት አውሮፕላን ነበረች። ይች አውሮፕላን ከጅቡቲ ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ የገባችው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።
በወቅቱ አውሮፕላኗ “ንስረ ተፈሪ” የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን፤ በወራት ልዩነት ውስጥ አንድ የጀርመን ስሪት ዡንክርስ (Junkers W33C) አውሮፕላንና ሁለት ተጨማሪ ፓቴዝ 25-A2 አውሮፕላኖች እንዲገቡ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን አውሮፕላኖችን የመጨመርና ኢትዮጵያዊያን አብራሪዎችን ለማፍራት በነበራቸው ፍላጎት ምክንያት፣ ፊያት ሞዴል ኤ.ኤስ.1 የሆነች የማስተማሪያ አውሮፕላን ታህሳስ 20/1922 ዓ/ም አዲስ አበባ እንዲገባ ሆነ።
አዲስ አበባ የገባችውን አውሮፕላን በመጠቀምና በኢትዮጵያ የአውሮፕላን አብራሪነት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያና ፈር ቀዳጅ የሆኑ ሰባት ኢትዮጵያዊያን የበረራ ተማሪዎችን በመመልመል፣ ከኢትዮጵያ የመጀመረያ የሆነችውን አውሮፕላን ከጅቡቲ አዲስ አበባ ድረስ እያበረረ በመጣው፣ በፈረንሣያዊው መሴ ማዩ አስተማሪነት የበረራ ትምህርቱ አቃቂ አካባቢ ተጀመረ፡፡
ኢትዮጵያውያን የበረራ ተማሪዎቹ ከአስር ወር በኋላ ለሚደረገው የንጉሱ የንግስ ቀን ክብረ በዓል ላይ የበረራ ትርዒት ለማሳየት በነበረው ፍላጎት ፣የበረራ ስልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰጥቶ ለማብቃት እንዲቻል ጋስቶን ቪዳል የሚባል አዲስ ፈረንሣያዊ ኢንስትራክተር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደረገ። ወቅቱ ክረምት በመሆኑ አዲስ አበባ የነበረው የበረራ ስልጠና ከሰኔ 5/1922 ዓ/ም በጅጅጋ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡

የበረራ አስተማሪው ጋስተን ደል ሁሉንም ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስመረቅ እንደማይችል በመገንዘቡ ከተማሪዎቹ ውስጥ በጣም የተሻለ ብቃት የነበራቸውን ሚሽካ ባቢቼፍና አስፋው አሊን በመምረጥ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በማሰልጠን ሚሽካ ባቢቼፍ እና አስፋው አሊ የመጀመሪያውን ሶሎ በረራ በጅጅጋ የመንግስት ሹማምንት እና ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት በየተራ አደረጉ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የበረራ ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ጥቅምት 4 ቀን 1923 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ሚሻክ ባቢቼፍ እና አስፋው አሊ ጃንሜዳ ላይ በተዘጋጀ ትልቅ መድረክ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ጨምሮ በርካታ ትላልቅ ባለሀብቶችና የውጪ ሀገር ዜጎች በተገኙበት ሚሻክ ባቢቼፍ እና አስፋው የተሳካ የአየር ትርዒት አቀረቡ። በእለቱም ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች የመቶ አለቅነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ሁኔታ የጀመረው የኢትዮጵያ የአቪዩሽን ታሪክ በተከታታይ ዓመታት ተጨማሪ አውርፕላኖች እንዲገቡ ሲደረግ ፣ የአብራሪዎች ቁጥርም በመጠኑ ለመጨመር ተሞክሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አንደ ሚሽካ ባቢቼፍ፣ ባህሩ ካባና ተስፋሚካኤል ኃይሌ የመሳሰሉ አብራሪዎችም በተከታታይ ወደ ፈረንሣይ አገር ለትምህርት ተልከው በተለያዩ የአቪዩሽንና የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጨማሪ ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
ተቋም በ1928 ዓ/ም የጣሊያን ወረራ ዋዜማ ላይ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አየር ኃይልን ለማቋቋም በማሰብ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች ውስጥ የተሻለ አውቀትና የበረራ ልምድ የነበራቸውን ሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍን ህዳር 20 ቀን 1928 ዓ/ም የአየር ኃይል አዛዥ አድርገው ሾሟቸዋል።
ሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍ ጥቅምት 4 ቀን 1901 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱ ሲሆን በአባታቸው በዜግነት ሩሲያዊ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ ተካበች ወልደፃዲቅ
የተባሉ ኢትዩጵያዊት ነበሩ፡፡ ሻለቃ ሚሽካ በበረራ ሙያ ችሎታ፣ በውጪ ሀገር የትምህርት አድል በማግኘት፣ እንዲሁም በወታደራዊ ማዕረግ ከአቻዎቻቸው ቀድመው የሻለቅነት ማዕረግ የተሰጣቸው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ ታሪክ አስረጂ ነው።
ከወረራው በኃላ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ለቃ ስትወጣ አየር ኃይልን በዘመናዊ መልክ መልሶ የመገንባት እንቅስቃሴ ከመጋቢት ወር 1936 ዓ/ም ጀምሮ በሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍ መሪነት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ ህዳር 21 ቀን 1937 ዓ/ም ሻለቃ ባቢቼፍ በሶቪየት ህብረት የኢትዮጵያ ኢምባሲ አንደኛ ጸሓፊ ሆነው በመመደባቸው ወደ ሞስኮ ሲላኩ ስዊድናዊው ካውንት ካርል ጉስታፍቭን ርዘን የአየር ኃይል አዛዥ ሆነው ተመደቡ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጉዞ ውስጥ በየዘመኑ በርካታ አዛዦች እየተቀያየሩ ተቋሙን መርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሁን ከደረሰበት የእድገት ደረጃ መሰረት የሆነዉ ከዛሬ 95 ዓመት በፊት ፓቲዝ 25-A2 የተሰኘች የፈረንሣይ ስሪት አውሮፕላን በኢትዩጵያ የአቪዩሽን ታሪክ ፈር ቀዳጅ በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ከገባችበት ከነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ/ም ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም፣ አየር ኃይል እንደ ተቋም ተመሰረተ ብሎ መውሰድ የሚቻለው ህዳር 20 ቀን 1928 ዓ/ም ንጉሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ኃይል አዛዥ ብለው ሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍን የመደቡበትና የተቋሙን መመስረት ያበሰሩበት እለት በበቂ ጥናት ተደግፎ የቀረበና በበላይ አካልም የፀደቀ በመሆኑ ነው።
ከባለፉት አመታት ጀምሮ 88ኛው፣89ኛ የምስረታ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት የተከበረ ሲሆን በዚህ ዓመትም 90ኛው ዓመት የአየር ኃይል የምስረታ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
በቀጣይነትም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስረታ ቀን በየዓመቱ ሲከበር ”ለታላቅ ሀገር የሚመጥን ታላቅ ተቋም” በሁለንተናዊ መልኩ የተገነባ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ይሆናል።
በዮናስ ጌታቸው





