ህልውና፣ ክብር፣ ነጻነት፣ እና ሉዓላዊነት እጅግም ረቂቅ ናቸው፡፡ ጥልቅ ናቸው፡፡ በእንቁ ስሌት አይተመኑም ፤በሚዛን አይቸረቸሩም፡፡ በወርቅ፣ በሸቀጥ አይለወጡም፡፡ አይመዘኑም፡፡ ድንግል፤ እምቅ፣ ዘመን ተሻጋሪ፤ ትውልድ አስረካቢ ተፈጥሯ አንጡራዊ ሀብት ናቸው፡፡
በአድርባይነት በባንዳነትም አይገኙም፡፡ ለባዕዳን በመንበርከክ፤ ጉልበት በመሳብ፤ ድራጎሽ ፍርፋሪ በመለቃቀም አይገኙም፡፡ ይልቁንም ከልብ በመነጨ ኢትዮጵያዊነት ይወለዳሉ፡፡
በላብና በደም እንጥፍጣፊ ነው የሚታነጹት፣ የሚገነቡት ተስፋ ያለው ትውልድ ለመፍጠርና ለማሻገር ነው፡፡ ሀገር የሚያጸኑትም በቁርጥ ቀን ልጆች በክፉ ቀን አይበገሬ ጀግኖች እጅግ ደማቅ፣ አኩሪና፣ ዘመን ተሻጋሪ መስዋዕትነት ነው፡፡

የወሎ እናቶች ሲተርቱ “ከልመና ደጃፍ አስመራ ቅርብ ነው!” ይላሉ፡፡ በሌሎች ይሁንታ የምትገኝ ነፃነት በፍጹም ከነጻነት ተርታ አትመዘንም፡፡ ትርፏ ውርደት እንጂ፡፡ በልመና የሚመኙት በድራጎሽ የሚገኝ ክብር ከክብሮች ሁሉ ተርታ ድርሽ አይልም፡፡ ትርፉ ህሊናን አንጠፍጥፎ መሸጥ፤ አንገት መድፋት ቅስም መሰበር እንጂ፡፡ ህሊናን ሸጦ በሌሎች ፈቃደኝነት መኖር እንጂ፡፡
በምጽዋት የሚገኝ ነጻነትና ክብር ከጅምሩ ፊት ያስገርፋል፡፡ ለዚያ ነው በልመና ወቅት ከፊታችን የቆመውን ሰው ፊት ከማየት ረጅም ሀገር ደርሶ መመለስ፤ ረጅም መንገድ መመታት ትንሽም በራስ ጥረት ሰርቶ አፍርቶ ክብርን መቋደስ ይቀላል የሚሉት አበው፡፡
ስለዚህ ሉዓላዊ ህልውናችን፣ ነጻነታችን ብሎም ክብራችን በክንዳችን፣ በኅብረታችንና በአንድነታችን መጽናቱ ግድ ነው፡፡ ክንዳችን በራሳችን ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ሳይንሳዊ ሀሳብና ጥበብ መደርጀት፤ መፈርጠምም አለበት፡፡ ህብረታችንን በተከታታይ የግድ ማፈርጠም የሚኖርብንም ዘመንን ጠላቂ፤ ትውልድ አቃፊ ርዕይ ስላለን ነው፡፡

አንድነታችን ከአለት የደደረ መሆን ያለበት በፈተናዎች ጊዜ ሁሉ በዓለም አደባባይ ብዙ ጊዜ በተከታታይ ዓለም ኢ-ፍትሃዊ መሆኗን ስላረጋገጥን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዋ ጣሊያን በተወረረች ጊዜ ብዙ ተገፍታለች፡፡ መንግስታችን የኢትየጵያ ክብር በዓለም የፍትህ መርህ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል ባለች ጊዜ ፍትህ ተነፍጎታል፡፡ ሁነኛ ወዳጅ ርቆበታል፡፡ በዚያም ጊዜ የኢትዮጵያውያን ዋነኛ መተማመኛ የውስጥ አርበኝነታችን፣ ጽናትና ጀግንነታችን ብሎም የባዕዳንን የበላይነት ቅስም የሰበረው ድላችን ነበር፡፡
እንዲሁም ከጽንሱና ከውልደቱ ጀምሮ የውጭ ኃይሎችን ኢትዮጵያን የማዳከም፣ የማፍረስና እንደ ሀገር ህልውና እንዳይኖራት የማድረግ ሴራ ሲያስፈጽም የኖረው ህወሐት የህልውና ስጋት በደቀነብን ጊዜ የዓለም ኢ- ፍትሀዊነት በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡
ሉዓላዊነት ኢትዮጵያ በታላቁ የዓለም መድረክ ከፍ ያለ ተሰሚነት፣ ፍትህና ክብር ልታገኝ ሲገባ ዓለም ለባንዳዎችና ቅጥረኞች ፍርደ ገምድል ነበረች፡፡ በዚህም ጊዜ በእልህ፣ በቁጭት፣ በተስፋ፣ በአንድነት፣ በህብረት በጽናትና በጀግንነት መቆም ነበር ዋስትናችን፡፡ ይህን በድፍረትና በወኔ በማድረጋችን የዓለም ፍትህ በራሷ አፍራለች፡፡ ተዋርዳለች፡፡ ክብራችን እንደ ከዋክብት ሲያበራ የዓለም ፍትህ በራሷ ዳካማ ሻማ ጭል ጭል ስትል ኮስምና ታይታለች፡፡
በመሃመድ ሙሳ
