የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንቦት 07 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ሚናዋን አዘምና ለመቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኗን የመከለካያ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። በሚኒስትሯ የሚመራው የልዑካን ቡድን በተመድ ሰላም ማስከበር የሚኒስትሮች ሰብሰባ ላይ በመካፈል ላይ ይገኛል።
በኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራው የልዑካን ቡድን በጀርመን በርሊን እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በመካፈል ላይ ይገኛል፡፡ ስብሰባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተግባራትንና አፈፃፀሞችን፣ የአቅም ክፍተቶችና በተልዕኮ ውጤታማነት ላይ ያተኮሩ ሪፎርምችን በተመለከተ ጥልቅ ውይይት የሚካሄድበት
ነው፡፡
በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ያላትን ዘመናትን የተሻገረ ቁርጠኝነት በማረጋገጥ በሰላም ማስከበር ስራዎች ተሳትፎዋን አዘምና እና አጠናክራ ለመቀጠል ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተግባራት የፋይናንስ ድጋፍ መቀነስ፣ የሰላም ማስከበር የአፈጻጸም ጥራት እና ታማኝነት መጓደል እንዲሁም ሰላም ማስከበር የሚካሄድባቸው አገራት እንደ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን አለማጉላት ችግሮች አፅንኦት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዲሲፕሊን፣ በቁርጠኝነትና ሙያዊ ብቃታቸውን በማስመስከር ብሎም ከህዝብ ጋር ከፍተኛ ትስስር በመፍጠር ግዳጃቸውን በመፈጸም ረገድ አኩሪ ስም አትርፈዋል ያሉት ሚኒስትሯ አገራቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ከተቀላቀለችበት ጊዜ አንስቶ ቀዳሚ
አስተዋፅኦ እያበረከተች ያለች መሆኗን ገልፀው ፤ በቀጣይም ይህንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴት ሰላም አስከባሪዎችን በማሰማራቷና በውጤታማነቷም ኩራት ይሰማታል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሚኒስትሯ በሰብሰባው ላይ እየተካፈሉ ከሚገኙት የእንግሊዝ ልዑካን ቡድን መሪ እና parliamentary under-secretary of state for the armed forces ከሆኑት ሚስትር ሊክ ፖላርድ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በሰብሰባው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የተመድ አባል አገራት በቀጣይ ለተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቃል እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ