የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለጦር በኤፍራታና ግድም ወረዳ ዳጉች የሚባል አካባቢ በመመሸግ ህዝቡን ሲዘርፍና ሲያሰቃይ በነበረዉ የፅንፈኛ ቡድን ስብስብ ላይ በወሰደው እርምጃ በቅፅል ስሙ ቀጭኔ በመባል የሚታወቀዉን የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ከነ ጀሌዎች ጭምር በመደምሰስ ቀሪዎችን ማርኳል፡፡
ክፍለጦሩ በፅንፈኛው ላይ በወሰደው እርምጃ የፅንፈኛውን አባላት ጨምሮ ከህብረተሰቡ የተዘረፈ አንድ አይሱዙ ተሽከርካሪ፣ የተለያዩ ዓይነት መሣሪያ እና ተተኳሽ በቁጥጥር ስር አውሏል።

የኮማንዶ ክፍለጦር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል አበባዉ ሞላ አፕሬሽኑ የተፈፀመዉ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ገልፀዉ ቡድኑ በዚህ ኦፕሬሽን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በተከታታይ በተወሰዱበት እርምጃዎች አከርካሪዉ ተሰብሮ አለኝ የሚለዉ መዋቅሩ ፈራርሶ የፌስቡክ አርበኛ ሆኖ መቅረቱን ተናግረዋል።
የሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ተስፋየ በላይነህ ፣ ሻለቃ ግዛቸዉ ዘሪሁን እና ሻምበል ግዛቸዉ ጊሎ እንደገለፁት ግዳጁ የተፈፀመበት አካባቢ የተፈጥሮ መሰናክል የበዛበት ለሰራዊቱ አመቺ ያልሆነ መልክዓ ምድር ቢሆንም ሠራዊቱ ፈታኝ የነበረውን የተፈጥሮ መሰናክል ሁሉ በማለፍ ስኬታማ ስራ መስራት ችሏል፡፡
ቀጣይም የፅንፈኛው ስብስብ ወደ ሠላም እስካልመጣ ድረስ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የህዝብን ሠላም ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ኮሎኔል አበባው ሞላ ተናግረዋል። ዘገባው የክፍለጦሩ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ነው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ