የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
በሁሉም የጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞን ተሰማርተው ግዳጃቸውን እየፈፀሙ ያሉ የሠራዊት ክፍሎች የፅንፈኛው ሃይል በቀቢፀ ተስፋ ዘመቻ ለአንድነት ብሎ ባደረገው ትንኮሳ ሠራዊቱ ፅንፈኛውን በመደምሰስ አገራዊ ግዳጁን በሚገባ እየተወጣ ይገኛል፡፡
በጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞን ስምሪት ላይ ያለው ሠራዊት እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሃይል በመቀናጀት ከመጋቢት 10 እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባደረጓቸው የተቀናጀ ዘመቻ የፅንፈኛውን ሃይል ህልም በማምከን በርካታ ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ ትልቅ ድል ተመዝግቧል።
የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ቀደም ሲል ፅንፈኛው ሃይል ላይ ባረፈበትጠንካራ ምት ከህዝብ በመነጠሉና ህልውናው ያከተመ በመሆኑ በሚዲያ አለሁ ለማለት ያክል በሁሉም የግዳጅ ቀጠናዎች ዘመቻ ለአንድነት ብሎ ትንኮሳ ቢፈጥርም ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን ባደረግነው የተቀናጀ የፀረ-ማጥቃት ጠላትን ሙትና ቁስለኛ በማድረግ አመርቂ ግዳጆችን ተወጥተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በፅንፈኛው ቡድን አደረጃጀት መሰረት 05 መካከለኛ የጠላት አመራርና በርካታ አባላቶች በዕዙ ሠራዊት ከፍተኛ ምት ተደምስሰዋል። የፅንፈኛው ሃይል አባላት 223 ሲደመሰሱበት 48 የቆሰለና 03 የተማረከ እንዲሁም 47 የፅንፈኛው አባላት የደረሰባቸውን ምት ባለመቋቋማቸው እጃቸውን ለሰራዊታችን መስጠታቸውን ጠቁመው ሠራዊታችን ባደረገው ስምሪት ብሬን በማውደም፣ 82 የነፍስ ወከፍ መሳሪያ፣ 06 ቦምብ፣ 06 ሽጉጥ፣ 02 የመገናኛ ሬድዮ፣ o6 ትጥቅና 265 የክላሽ ብትን ጥይት መማረካቸውን ገልፀዋል፡፡
ለፅንፈኛው ሃይል ሊሰጥ የነበረ በአንድ ተሸከርካሪ የተጫነ የተለያዩ ወታደራዊ አልባሳቶች፣ የመገናኛ ሬድዮኖችና ተተኳሾች ሙሉ በሙሉ በማውደም የጠላትን እኩይ ሴራ ማምከን መቻሉን የገለፁት ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ በቀጠናው ፅንፈኛው የሚገለገልባቸው ሞተር ሳይክል፣ መድሃኒትና በርካታ ሊትር ቤንዚን በሰራዊታችን ቁጥጥር ስር ማዋል ተቸሏል ብለዋል።
ፅንፈኛው ሃይል የሰራዊታችንን ጠንካራ ምት መቋቋም ባለመቻሉ እየተበታተነና እየፈረጠጠ በመሆኑ ሰራዊታችን ጠላትን እግር በእግር በመከታተልና በማሳዳድ የመደምሰስ ግዳጃችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ለቀጠናው አንፃራዊ ሰላም መምጣት የክልሉ የፀጥታ ሃይል፣ህዝቡና አመራሩ በመቀናጀት የሰሩት ስራ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ቀጣይም በጋራ በመሆን የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ተቀናጅተን እንሰራለን ሲሉ ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡
በአወል መሃመድ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ