የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
የሙስና ወንጀል በማንኛወም የስራ ዘርፍ ላይ ሊከሰት እና ሊያጋጥም የሚችል ወስብስብ ዓለማቀፋዊ እና ሀገራዊ ስጋት ያለው እና ለሀገር ዕድገት እንቅፋት የሆነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመከላከያ ስነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት “ሙስናን በመከላከል የዜግነት ግደታየን እወጣለሁ” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ መከለከያ መረጃ የሠራዊት አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የመከላከያ ስነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት የሙስና መረጃ ትንተና ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ሺሻይ ተስፋሁን ሙስና በየትኛውም የስራ መስክ ላይ በስውር እና በረቀቀ መንገድ ሊፈፀም የሚችል ወስብስብ ወንጀል በመሆኑ ዓለማቀፋዊ እና ሀገራዊ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

ወንጀሉን ውስብስብ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ የሙስና ወንጀል ሲፈፀም ጉዳቱ በቀጥታ በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ አለማረፉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም በሚል የተሳሳተ ሀሳብ ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል ቸልተኝነቱ እየበዛ በመምጣቱ ወንጀሉ እየተስፋፋ በዓለም ደረጃ አሁን ከደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
የስልጠናው አስተባባሪ የኢትዮጵያ መከላከያ መረጃ ስልጠና ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ያሬድ ሰለሞን የሰራዊቱ ቁልፍ ተግባር የሀገርን ዳር-ድንበር በመጠበቅ የህዝቦቿን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ማቆም ቢሆንም በየሚሰማራባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ባላማወቅ ለቀላልም ሆነ ለከባድ የሙስና ወንጀሎች ተጋላጭ እንዳይሆን ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ሀገሩን በፍቅር የሚያገልግል እና በስነ-ምግባር የታነፀ ወታደር እንዲቀረፅ ሁሉም የተቋሙ አባል የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በማደረግ በኩል የራሱን ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
በብርሃን እንዳየሁ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ