የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም
መከላከያ ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለሀገር በሚል ቁልፍ እሴት ወስጥ ሆኖ ለሀገር እየከፈለ የሚገኘውን ውድ ዋጋ ግምት ውስጥ ያስገባ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለፁ።
የመከላከያ ሠራዊቱን ሁለንተናዊ አቅምን ማሳደግ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስከበር በሀገር እና በህዝብ ህልዉና ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን እና ስጋቶችን በማስቀረት ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃትና በአስተማማኝ ደረጃ ለመፈጸም እንዲያስችለው ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ ኢንተርፕረነርሺፕ እና ኢኖቬሽን ማዕከል መመስረት መከላከያ ከሪፎርም ወደ ትራንስፎርሜሽን መሸጋገሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገልጸዋል።
የዚህ ማዕከል መመስረት ለሀገር አንድነት እና ሉአላዊነት መከበር ሲሉ ውድ ዋጋ በመክፈል በክብር የተሰናበቱ እንደዚሁም ለተሰዉ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤተሰቦችን ቀጣይነት ባለው መንገድ ራሳቸውን ችለው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እና ተጨማሪ ሀገራዊ አቅም እንዲሆኑ በማስቻል በኩል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናግረዋል።
በሁሉም የመከላከያ ክፍሎች እየታዬ ያለው የስራ ተነሳሽነትና ውጤት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በቀጣይነትም ከዚህ በላይ ውጤት ለማሥመዝገብ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። እየተመሠረተ ላለው ማዕከል የሠራዊቱ ድጋፍ የገቢ ምንጪ መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለማዕከሉ መመሥረት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያበረከቱትን አሥተዋፅኦ አድንቀው በሌተናል ጄኔራል ይመር መኮነን የተመራው አዘጋጅ ኮሚቴ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በወንድማገኝ ታደሠ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/ fdredefense.official