የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ ዕዙ የጥፋት ሃይሎችን ተከታትሎ የመደምሰስ ስምሪት በወሰደበት ቀጠና ላይ ተገኝተው የጋሻ ኮር ሬጅመንቶች በተሰማሩበት አካባቢ በመዘዋወር የሰራዊቱን ግዳጅ አፈፃፀም በመመልከትና ጀግንነቱን በማበረታታት “የድል ሠራዊት!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን 119ኛውን የሰራዊት ቀን ከክፍሉ አባላት ጋር አክብረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃያል ክንዱ የሆነውን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የቀደምቶቹን ጀግንነት ያስቀጠለ ክንደ ብርቱ የሰላም ተመራጭ ሀይል መሆኑን የገለፁት አዛዡ የወራሪን ቅስም በመሰባበር የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ ሉአላዊነቷን ያስከበረች ሀገር ለትውልድ የማሻገር ታሪካዊ ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከአያት ቅድመ አያቶቹ የተረከበውን አኩሪ የጀግንነት ገድል ጠብቆ እያሻገረ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከየአቅጣጫው ተሰባስቦ የገጠመውን ጠላት ድል እየነሳ በሚገኝበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ሆኖ ድል አድራጊነቱን በተግባር የሚዘክር የሃገር ብርቱ ክንድ አስተማማኝ የድል ሰራዊት ነው ብለዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከጥንት እስከ ዛሬ ሀገራችንን ሲፈታተኑ የነበረ ቢሆንም በየዘመናቱ በተፈጠሩ ጀግኖች ተጋድሎ ምኞታቸው ከስሟል ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ራሱን ከዘመን ጋር እያዘመነ ባላንጣዎቹን እንደ አመጣጣቸው በማስተናገድ ሁሉንም ፈተናዎች ተጋፍጦ ፈታኞቹን ድል ማድረግ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
“የድል ሰራዊት” በሚል መሪ ቃል ለ119ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰራዊት ቀን በማስመልከት በተዘጋጀ ፅሁፍ ላይ ሬጅመንቶት ላካሄዱት የፓናል ውይይት የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት ጀኔራል መኮንኑ እንደሰራዊት በቀጣይ የሚኑሩት ወሳኝ ምዕራፎች የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ህልውና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በመጠቆም ከዚህ በላይ መፅናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
