ዓላማችን የዘመኑ አርበኛ ሆነን እዚህ የደረሰችውን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሰሜን ምዕራብ ዕዝ አመራሮች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ በሰጡት የስራ መመሪያ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ በክብር ያቆዩ አርበኞች ናቸው፤ ሠራዊታችን ደግሞ የዚህ ዘመንና ትውልድ አርበኛ ነው ብለዋል።
ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በአገራዊ ለውጡ ማግስት የተመሰረተ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ራሱን እያደራጀና እያጠናከረ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየፈፀመ የመጣ ዕዝ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አገር ለማሻገር ከባንዳ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ የጀግንነት ታሪኩን በደማቁ የፃፈ ዕዝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በጎንደር ፤በወልቃይት ጠገዴ፤ በኤርትራና ሱዳን ደንበር አካባቢ ያለውን ወስብስብ ግዳጅ ለምንም ነገር ሳይበገር ተልዕኮውን በፅናት የተወጣ ዕዝ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
እንደ ሃገር የተጀመሩ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ይጠበቅባችኋል ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ክፍተቶቻችሁን በመሙላት ለቀጣይ ግዳጅና ተልዕኮ የበለጠ መዘጋጀት ይጠበቅባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።
ዘገባው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ነው።