የምስራቅ ዕዝ አዛዥ እና የጎጃምና የደቡብ ጎንደር ጸጥታ ካውንስል ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ከዕዙ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ዋና አዛዡ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደርና በጎጃም ዞኖች ተሰማርቶ ጽንፈኛውን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ቀጠናው የተረጋጋ እንዲሆን ሠራዊቱ በርካታ ግዳጆች መፈፀሙን ገልፀዋል። ከፍተኛ አመራሮቹ እስካሁን በተደረጉ ኦፕሬሽኖች ያስመዘገቧቸውን ድሎች በማጎልበት በማንኛውም ሰዓት መከላከያ ለሚሰጠው ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ምስራቅ ዕዝ እስከ አሁን ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በድል እየተወጣ የመጣና የኢትዮጵያ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች የሚሸርቡትን ሴራ እያከሽፈ ተላላኪዎቹን በመደምሰስ ዕዙ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣቱን አስገንዝበዋል።
የዕዙ አመራሮች የተቋማችንን ቁልፍ ተግባራት በማከናወን ፣ አሁን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ፣ ሠራዊቱን በተደራጀ መንገድ የአሸናፊነትን መንፈስ ማላበስ እንደሚገባቸው የተናገሩት ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ባገኘናቸው ድሎች የተሞክሮ ልውውጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ለቀጣይ የግዳጅ አፈፃፀም አገራዊ አስተሳሰብን እና ውስጣዊ አንድነትን እያስጠበቅን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።
ምስራቅ ዕዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ የራሱን የማድረግ አቅም እየገነባ እና እያደረገ ያለውን የህግ ማስከበር ሕገ-መንግስታዊ ሀላፊነቱን አጠናክሮ በመቀጠል የአማራ ክልልን ሰላም ይበልጥ ለማረጋገጥ ከክልሉ መንግስት እና ህዝብ ጋር መሥራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘጋቢ ታደሰ ይሴ
ፎቶግራፍ ማሩፍ ደስታ