በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሥር የሚገኘውን የዚህን ተቋም ሁለገብ የእንቅስቃሴ ሂደት የተመለከቱት የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ፤ ኢንዱስትሪው ከነበረበት ደረጃ ተነስቶ አሁን ላለው የትርፋማነትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነት የበቃው በአመራሩና በሠራተኛው ቁጭት በተወለደ ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት መሆኑን ገልፀዋል።

ተቋሙ የላቀ ቴክኖሎጂ የታጠቁና ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ወታደራዊ ምርቶችን በማምረት የመከላከያ ሠራዊቱ የጀርባ አጥንት መሆኑን ያሰመሩበት ሚኒስትሩ፣ የለውጥ ጎዳናውን ይበልጥ ለማስቀጠል የቅርብ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለፅ የምርት ጥራትና የቴክኖሎጂ ዕድገቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የተገኙት የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የለውጥ ማዕከል ሆኖ በመገኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ በተለይም በሴት ሠራተኞች ዘንድ የታየው የይቻላል መንፈስ የሚያኮራና ለሌሎችም በአርአያነት ሊወሰድ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
