የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ እና የመከላከያ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማዕከል የሠራዊት አባላት ጥቅምት 24 ዝክረ ሰሜን ዕዝ በተለያዩ ዝግጅቶች አስበው ውለዋል።
“እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን” በሚል መሪ ቃል የታሰበው ዝክረ ሰሜን ዕዝ ሰራዊታችን በክሃዲ ሀይሎች ከጀርባው የተወጋበት ዕለት በመሆኑ ሁሌም ስንዘክረው የምንኖር የታሪካችን አንዱ አካል ነው።

በዚህ የመታሰቢያ ቀን ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ጀኔራል ደስታ አብቼ ህወሃት ሰው የመብላት ታሪኩ ከበረሃ የጀመረ እንደነበረ በመግለፅ በዚህም አብረው የሚታገሉትን ድርጅቶች ሳይቀር ወዳጅ መስሎ እንደጨረሳቸው አውስተዋል።
ሰራዊታችን በትግራይ ምድር በቆየባቸው ዓመታት ያልሰራው መልካም ተግባር አልነበረም ያሉት ጀኔራል ደስታ አብቼ ይህ የደግነት ተግባር ውለታ በተኛበት መውጋት መሆኑ እጅግ የሚንገበግብ ነው ብለዋል።
ህወሃት ስልጣን በያዘ ማግስት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት አድርጎ የቆለፈ በህዝብ ዘንድ ክፍፍል እንዲኖር የተቻለውን ሁሉ የሠራ መሰሪ ቡድን ሥለመሆኑም ገልፀዋል።
የሠራዊቱ ዝግጁነትና አቅም ምንጊዜም በጀግንነቱ ይረጋገጣል ያሉት ጀኔራል ደስታ አብቼ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟ እንደተከበረ እንዲቀጥል ሰራዊቷ ዘመኑን በዋጁ ትጥቆች እየተደራጀ መሆኑንም አንስተዋል።

በመጨረሻም እኛ እንደ መከላከያ ተቋም ጥቅምት 24ትን መቼም የትም ሆነን አንረሳውም በማለት ጓዶቻችን በግፈኞች ዋጋ የከፈሉላትን ሀገር የማስቀጠል አደራችንን በሚገባ እንወጣለን ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በዕለቱ በመከላከያ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የተዘጋጀ ዕለቱን የሚያስብ ዶክመንተሪ የቀረበ ሲሆን ግጥም የማቅረብ እና የጧፍ ማብራት ሥነ ሥረዓት በመርሃ ግብሩ ተካቷል።
