የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በደብረ ብርሃን ፣ በህዳሴ ግድብ እና ቢሾፍቱ በሚገኘዉ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲሁም አዲስ አበባ በሚገኘው ጠቅላይ መምሪያው አዛዡን ጨምሮ ሌሎች የየክፍሉ አመራሮችና አባላት በተገኙበት 6ኛ ዓመት ዝክረ ሰሜን ዕዝ ታስቧል።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ የሰሜን ዕዝ በወቅቱ ስለከፈለው መስዋዕትነት እና ተጋድሎ ያወሱ ሲሆን በከሀዲዎቹ ህወሃት የተፈፀመበትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም አንስተዋል።

ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ያንን ጊዜ የምናነሳው በደልን ለመቀስቀስ ወይም ቁስልን ለመነካካት ሳይሆን የተፈጠረው ነገር በቀጣይ እንዳይደገም ትምህርት መዉሰድ ስለሚያስፈልግና ግፍ የተፈፀመባቸውን ሰማዕታትን መዘከር ስለሚገባ እንደሆነ ብሎም መረሳት የሌለበት ጥቁር የታሪካችን አካል መሆኑን እንድናዉቀዉ ነው ብለዋል።
በተደጋጋሚ ሀገር ለማፍረስ የሄደበት እርቀትና ክህደት በጀግናው መከላከያ ሰራዊት እና በህዝባችን ድጋፍ መክሸፉን ያነሱት አዛዡ የትግራይ ህዝብን በግዞት ይዞ ሲያሰቃየዉ የኖረ መሆኑንም ገልፀዋል።
ሠራዊቱ እስከመጨረሻው ታግሎ የሀገሩን ሰላምና መረጋጋት እንደሚያረጋግጥ የገለፁት ቫይስ አድሚራል ክንዱ የባህር ሃይል አባላት የተሠጣቸውን ማንኛውንም ተልዕኮ በድል ለመውጣት ዝግጁነታቸውን በሁሉም መስክ ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል። ዘገባው የባህር ኃይል የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ነው
