የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክን በፅሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ እና በወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።

በውይይቱ ወቅት አቶ መሐመድ እድሪስ፤ ፈረንሳይ አሁናዊ እና ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ አቅምን ለማሳደግ እያደረገች ላለችው የአውቀት ሽግግር እና የሰላም ማስከበር ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር እያደረገች ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ፍትሀዊ እና ህጋዊ ጥቅሟን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ ከጎኗ እንድትቆምም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን የመልሶ ማቋቋምና የሠራዊት ማዋሃድ (DDR) ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ፈረንሳይ ለሂደቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነትና ሁለገብ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የገለፁ ሲሆን፤ በተለይም በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም በወታደራዊ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፎች የሚከናወኑ የጋራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ነው
