ከሃዲው ህወሃት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን ክህደት መቼም ቢሆን አንረሳውም ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ።
“እንዳይደገም መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል ዝክረ ሰማዕታት ሰሜን ዕዝ 6ኛ ዓመት መታሰቢያ በሰሜን ምዕራብ ዕዝ፣ በ10ኛ ዕዝ፣በ5ኛ ሜካናይዝድና በስትራቴጂክ መሳሪያዎች ኮር እንዲሁም በጠቅላይ መምሪያ ስታፍ ከምስራቅ ዕዝ አባላት ጋር በጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት ታስቧል።
የሰሜን ዕዝ በከሃዲያን የተፈፀመበት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን መቼም ቢሆን አንረሳውም ያሉት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ሰማዕታት ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ ብለዋል።

ጥቅምና ስልጣን የመፈለግ አባዜ የተጠናወተው ከሃዲው የህወሃት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን የሀገር ባለውለታ የሆነውን ሠራዊት ከጀርባ በመውጋት በዓለም ተፈፅሞ ያማያውቅ አስነዋሪ ድርጊትን የፈፀመ ነው ብለዋል ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ።
ዕለቱን ስናስብ በሠራዊታችን ላይ የተፈፀመው ክህደት መቼም ቢሆን እንዳይደገም ለማስታወስና ክቡር ሰማዕታትን ለመዘከር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተከብራ ትኖራለች ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ቀጣይ ለሚኖረን ተልዕኮ የበለጠ በመዘጋጀትና የጀግኖች ሰማዕታትን አደራ በፅናት በመፈፀም ነው ሲሉም አሳስበዋል።
