ኮሪያ በወረራ ጥቃት በደረሰባት አስቸጋሪ ወቅት ለኮሪያ ለከፈላችው ውድ ዋጋ እናመሰግናለን፤ ዛሬ እዚህ የተገኘነው ይህን ታሪካዊ ውለታ ለማመስገንና የቃኘውን ወንድማማችነት ይበልጥ ለማስቀጠል ነው ሲሉ የደቡብ ኮሪያ የምድር ጦር ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሊ ዉ-ሄዎን ተናግረዋል።
ሜጀር ጄነራል ሊ ዉ-ሄዎን ይህንን የተናገሩት በኮሪያ ጦር ሠራዊት አስተባባሪነት የታደሱ የሁለት የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች መኖሪያ ቤቶች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአካል ተገኝተው ነው።

አዛዡ በንግግራቸው የደቡብ ኮሪያ ህዝብና መንግስት በጦርነቱ ወቅት መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ህዝቦችና የቃኘው ሻለቃ አባላት ያላቸውን የከበረ ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ በደም የተሳሰረ ወንድማማችነት ወደፊትም በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ሜጀር ጄነራሉ በዘመቻው ለተሳተፉ ዘማቾች የሚደረገው የጤና እና የኑሮ ድጋፍ እንዲሁም ለልጅ ልጆቻቸው የሚሰጠው የነፃ ትምህርት እድል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ከቤት ምረቃው አስቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የጦር አዛዦቹ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ሙዚየም የጎበኙ ሲሆን ለኮሪያ ህዝብ ህልውና ሲሉ ለወደቁት የቃኘው ሻለቃ ሰማዕታት አበባ በማስቀመጥ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።

በመቀጠልም በሰበታ እና በኮተቤ የካ ክፍለ ከተማ የሚገኙትን የታደሱ የሁለት ዘማች መኖሪያ ቤቶችን በይፋ መርቀው አስረክበዋል።
ኮሪያ ለኢትዮጲያ ሁለተኛ ቤታችን ናት ያሉት የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል ኢትዮጵያ በኮሪያ ያደረገችው ተሳትፎ በታሪክ ማህደር ውስጥ ደምቆ የሚኖር መሆኑን ገልጸው ኮሪያውያን ከዛ ጊዜ ጀምሮ ለዘማቾቻችን የሚያደርጉት የጤና፣ የኑሮ እና የቤት እድሳት ድጋፍ እውነተኛ ውለታ መላሽነታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከደቡብ ኮሪያ ድረስ በአካል በመምጣት የተደረገው ይህ ድጋፍ በሁለቱ ሀገራት ሠራዊትና ህዝቦች መካከል በደምና አጥንት የተገነባውን ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ ያረጋገጠ መሆኑንም አክለዋል።
የቤት እድሳት የተደረገላቸው የአራተኛ ቃኘው ዘማች ወታደር ንጉሴ አርጋው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኮሪያ ዘመቻ ያሳየችው ጀግንነትና አለኝታነት ዛሬ ላይ ወዳጅነታችንን ይበልጥ ያቀራረበ ተግባር ነው በማለት ለተደረገላቸው የቤት ዕድሳት ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የኮሪያን ባህላዊ እሴት የሚያንጸባርቅ የምስጋና መግለጫ ስጦታም ለኮሪያ ዘማቾች የተበረከተ ሲሆን፤ ይህ ስጦታ በሙዚየሙ ተቀምጦ የሁለቱን ሀገራት ዘላቂ ወዳጅነት የሚያሳስብ ታሪካዊ ማስታወሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል አረጋግጠዋል።
