የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲወስዱ የቆዩት የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና ተጠናቋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሃላፊ ጀኔራል ይመር መኮነን ለተመራቂዎቹ ሰርተ-ፊኬት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከፍተኛ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብን በመማርና በመሠልጠን የመከላከያ ሠራዊቱን የሥራ ባህል፣ ዲሲፕሊን እና መርሆዎች እንዲያውቁ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
ከአካላዊና አእምሯዊ ዝግጁነት፣ ከቡድን ሥራ እንዲሁም ከስትራቴጂካዊ አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተግባራዊና ንድፈ ሃሳባዊ እውቀት ለማዳበር ያለመ ሥልጠና በመሆኑ፣ በሲቪል አመራርና በመከላከያ ተቋም መካከል የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከር የሚያግዝ ሥልጠና እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሮቹ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና መውሰዳቸው ሀገርን ወደ ተሻለ የዕድገት ጎደና ለማሻገር የሚያግዝ ነው ያሉት ጄኔራል ይመር መኮነን ከነበራቸው የስራ ባህል በተጨማሪ የወታደራዊ የስራ ባህልና ሀገር ወዳድነትን እንዲሁም እየሞቱ ሀገርን የማፅናት የውትድርና ሙያን ለመገንዘብ እንደሚረዳም አንስተዋል።
አመራሮቹ በስልጠናው ያገኙት ተሞክሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ተግባርና ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ አመራር ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በሁርሶ የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለከፍተኛ የሃገሪቱ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና የተቋሙን የማሠልጠን አቅምና ልምድ ያሳየ ተሞክሮ ነው። የከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና የወታደራዊ እውቀትን፣ የአመራር ብቃትንና የሀገራዊ ራዕይ ትስስርን ለማጉላት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ጄኔራል ይመር መኮነን ተናግረዋል።
የሥልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫጮ ከፍተኛ አመራሮች በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተከታተሉትን ስልጠና የሲቪል አመራሩ እና መከላከያ በጋራ የሃገርን ራዕይ ማሳካት የሚችሉበትን፣ የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የደህንነት ጉዳዮችን በተቀናጀ አመራር ለመምራት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
