የመርሳት በሽታ ምንድን ነው? ማንንስ ያጠቃል?
በየቀኑ ወደ አዕምሯችን የሚመጡትን መረጃዎችን አዕምሯችን መዝግቦ የትውስታ ማህደር ክፍላችን ውስጥ ማስቀመጥ ይኖርበታል ። ነገር ግን አዕምሯችን ይህንን ተግባር በትክክል ማከናወን ካቃተው ፣ አንድ ግለሰብ የተለመደ ስራውን ማከናወን ይቸገራል። ይህ ችግር ያለበት ግለሰብ የመርሳት ችግር እንዳለበት በማሰብ አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና ሊደረግለት ይገባል።
የመርሳት ችግር ብዙ ጊዜ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ቢሆንም አሁን ላይ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በየትኛውም እድሜ ክልል ሊከሰት እንደሚችል ነው። ይሁንና እድሜያቸው ከ65 አመት በታች የሆኑት ላይ ግን አነስተኛ ነው።
መንስኤዎች ፡-
• አልዛይመር (Alzheimer’s disease)
• የደም ግፊት ወይም መርጋት ህመም
• የHIV/AIDS ህመም
• አንጎላችን ተደጋጋሚ አካላዊ ጥቃት ሲደርስበት ለምሳሌ ጭንቅላታቸው በተደጋጋሚ የተመቱ ሰዎች
• የተለያዩ ሌሎች የአእምሮ ህመሞች በተለይ የድብርት
ህመም
• አካላዊ የህመም አይነቶች ምሳሌ የቫይታሚን ምግብ እጥረቶች፣ የእንቅርት ህመም፣ የተለያዩ የአንጎል እጢዎች
• ለረጅም ጊዜ ማጨስና የአልኮል መጠጥ ማዘወተር
• እንዲሁም በዘር የመጋለጥ ሁኔታ እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች የመርሳት ችግር ሊያመጡ ይችላሉ ።
ዋና ዋና ምልክቶች ፡-
• ያስቀመጡትን እቃ መርሳት
• በሂደት ቀጠሮ መርሳት ፣ እቃ ገዝተው መልስ አለመቀበል ፣የሚሰሩትን ስራ በአግባቡ ለመስራት መቸገር የመርሳት ችግሩ እየባሰ መምጣት
• የቅርብ ጊዜ ክንውኖችን አለማስታወስ ወይም አዲስ መረጃ መያዝ አለመቻል፣ እየቆየ ሲሄድ ራቅ ባለጊዜ የተከናወነውን ጭምር መርሳት ይመጣል
• ኑሯቸውን በእቅድና በማስተዋል ለመምራት መቸገር
• ዘዋሪ መሆን ወይም አላማ የሌለው እንቅስቃሴ ቤት አካባቢ ወይም ከቤት ውጪ ሲያደርጉ መስተዋል
• በቀላሉ ቁጡ መሆን፣ መነጫነጭ
• ዝምታን መምረጥ ፣የመከፋት ወይም የመጨነቅ ስሜት ማሳየት
• ተጠራጣሪ መሆን
• በህይወት የሌሉ ሰዎችን አብረው እንዳሉ ማሰብ
• እንቅልፍ በአግባቡ አለመተኛት ወይንም የእንቅልፍ ሰአት መዛባት
ህክምናው እና ጠቃሚ ምክሮች ፡-
አንድ የቤተሰብ አባል በመርሳት ህመም ሲጠቃ ግለሰቡን ለመርዳት ወይንም ራሳቸውን ካላስፈላጊ ጫና ለመጠበቅ የሚከተሉትን ነጥቦች መሞከር ያስፈልጋል ምክንያቱም ጫናው እየበዛ ሲመጣ ጤናማ የነበሩትን የቤተሰብ አባላት ለድብርት ወይንም ለጭንቀት ህመም ሊጋለጡ ይችላሉ።
1.እንዲህ አይነት ችግር የተስተዋለበት ሰው ቶሎ ወደ ህክምና ቦታ መውሰድ
2. እንዲሁም ግለሰቡን የሚንከባከቡ ሰዎች ቶሎ ቶሎ ባይቀያየሩ፣የሚኖሩበት ክፍል የበዛ ብርሃን ባይኖረው እንዲሁም ጫጫታ የማይበዛበት ቢሆን ይመረጣል
3-የማታ እንቅልፋቸው ለማሻሻል ቀን ላይ እንዳይተኙ ፣ የሚያነቃቁ ነገሮችን እንዳይወስዱ ፣ሞቅ ባለ ውሃ ገላቸውን እንዲታጠቡ ማድረግ
4-በተጨማሪም የተዛባ የእንቅልፍ ሁኔታ፣ አግባብነት የሌለው የበዛ ጥርጣሬ ፣ ብስጩነት፣ እንዲሁም ከላይ የተዘረዘሩት መሰል የባህሪ ለውጦችን በመድሃኒት ማሻሻል ስለሚቻል ቶሎ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ያስፈልጋል።
