የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት ማህበራት ህብረት አራተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሌላ ሀገርን ለመውረር ያለመ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግና በዲፕሎማሲ አማካኝነት መፍትሄ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መሆኑን እና ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ካላገኘ ሀገራችን ያለአግባብ የተወሰደባትን የባህር በር ለማስመለስ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር መራቋ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ስብራቶች አንዱ መሆኑን እና በሴራና በተንኮል የባህር ኃይላችን እንዲፈርስ ብሎም የባህር በር እንድናጣ መደረጉም ሀገራችንን ለተለያዩ ተግዳሮቶች እንደዳረጋት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብቻ የተጀመረ እንዳልሆነ ያነሱት ቫይስ አድሚራል ክንዱ፣ ሀገራችን አሰብና ምጽዋን ጨምሮ ከቀይ ባህር ጋር የነበራት ታሪካዊ የንግድ ግንኙነት ከጥንታዊ ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ የሚዘልቅ መሆኑን አስታውሰዋል።
ተሰብሳቢዎቹ ሙሉ የህይወት ዘመናቸውን በውትድርና አገልግሎት ያሳለፉ በመሆናቸው አባላቱ በውትድርና አገልግሎታቸው ያካበቱት ልምድና ያሳረፉት ታሪካዊ አሻራ ለአሁኑና ለቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅም መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው በቀድሞውና በአሁኑ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር፣ የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግና የቀድሞ የጦር ኃይሎች አባላትን አስተዋጽኦ ለማስቀጠል ወሳኝ መድረክ መሆኑንም አዛዡ አመላክተዋል።
በመጨረሻም የቀድሞ የጦር ኃይሎች አባላት ለሀገር አንድነት የከፈሉትን ዋጋና ያስመዘገቡትን ታሪካዊ አሻራ በማድነቅ፣ ያካበቱት ልምድና የሀገር ፍቅር መንፈስ ለአሁኑ የባህር ኃይል ግንባታና ለቀጣዩ ትውልድ አርዓያ እንደሚሆን ገልጸው፣ ለጉባኤው ስኬታማነት ምስጋና አቅርበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህር ሀይል አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
