በደቡብ ሱዳን ደቡባዊ ሴክተር በጆንግሌ ስቴት የተሠማራው 22ኛው ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ በአስተማማኝ ሁለንተናዊ ወታደራዊ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (UNMISS) ገምጋሚ ቡድን አረጋገጠ፡፡
ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ሙያ ስፔሻሊስቶች የተውጣጣው ይህ ገምጋሚ ቡድን 22ኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ በተሠጠው ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁለንተናዊ እውቀትንና ክህሎትን፤ የግዳጅ አፈፃፀሙን፤ የእቅድ አዘገጃጀት እና የሪፖርት ስርዓቱን፤ ከበላይ እና ከበታች እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት እና ትስስርን ጨምሮ የዶክመንቴሽን ስርዓቱን ተዘዋውሮ ፈትሿል፡፡
የኢንስፔክሽን ቡድኑ አዛዥና የደቡባዊ ሴክተር ምክትል አዛዥ ለዘመቻ መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል አማር ባያስጋላን ሠላም አስከባሪ ሻለቃው በቅድመ ስምሪት ስልጠና ወቅት ስለሚሠጠው ተልዕኮ በቂ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል ትምህርትና ልምምዶችን ማድረጉን በመረዳት ይህንን አቅም በተሠማራበት ተልዕኮ እንዴት እየተጠቀመበት እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችሉ የቢሮና የመስክ ምልከታዎችን አድርገናል ብለዋል፡፡
የቡድኑ አዛዥ በተደረጉ ምልከታዎች ሠላም አስከባሪ ሻለቃው የተሠጠውን ተልዕኮ በግልፅ እንደሚገነዘብና አለም አቀፍ ህግና አሰራርን ተከትሎ ግዳጁን እንደሚፈፅም ማረጋገጣቸውን ገልፀው በእቅድ አዘገጃጀት፤ በሪፖርት ስርዓት፤ በግንኙነትና ዶክመንቴሽን ከፍተኛውን ነጥብ ማስመዝገቡን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች በዚህ አይነት ተልዕኮ የረዥም ግዜ ልምድ ያላቸው፤ ተልእኳቸውን ለመፈፀም ሁሌም ዝግጁ የሆኑ፤ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፉ፤ በጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተገነቡ፤ ለየትኛውም ተግዳሮት የማይበገሩና በትብብር መስራትን የሚያውቁ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ኢብራሂም ኢብሬን በበኩላቸው በሻለቃው ማዘዣ በመገኘት ወታደራዊ ዝግጁነትን ለማረጋገጥ ለመጣው የባለሙያዎች ቡድን ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው ቡድኑ ቢሻሻል መልካም ነው ያሉንን ጥቃቅን ነገሮችን በፍጥነት አሻሽለን የተሰጠንን የሃገር እና የህዝብ አደራ በአመርቂ ውጤት ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
