የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል፣ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጆሲ ማሲንጋን በፅሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ወቅት ክቡር ሚኒስትሩ ፤ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ጠንካራና በውጤት የታጀበ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጠና የመረጋጋት ምሰሶ መሆኗን ገልፀው ሁለቱ ሀገራት በቀጠናው መረጋጋት ላይ በቅርበት መስራታቸው ዘርፈ-ብዙ ውጤት ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
አክለውም በቅርብ ጊዜያት የሁለቱ ሀገራትን ስትራቴጂካዊ ወታደራዊ የስምምነት ማዕቀፍ መፈረም የአሜሪካ አምባሳደር እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለተጫወቱት የጎላ ሚና ምስጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የህዝቧን አሁናዊና ቀጣይ ፍላጎት ለመመለስ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምትጥር ሀገር መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ አሜሪካም በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተውን የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂክ አጋርነት መሰረት እያደረገች ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጆሲ ማሲንጋ በበኩላቸው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜና ከሁኔታዎች የተሻገረ መሆኑን ገልፀው፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥታ እንደምትሠራ አረጋግጠዋል።
አምባሳደሩ አክለውም በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመከላከልና በወታደራዊ ዘርፍ የተጀመሩ ስትራቴጂካዊ ትብብሮችን አሜሪካ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ገልፀዋል። ዘገባውን ያደረሰን የሚኒስትር ፅህፈት ቤት ነው
