ዕዙ በሚታወቅበት ጀግንነት ለማስቀጠል በቀጣይ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በድል ለመወጣት ሁለገብ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጄር ጄኔራል ሙላት ጀልዱ ተናግረዋል።
ጄኔራል መኮንኑ በምዕራብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ዴዴሳ ተገኝተው ከኮሮች የተወጣጡ የሬጅመንት አመራሮች እና የሻምበል አመራሮች እንዲሁም የቡድን መሳሪያ ሰልጣኞች የስልጠና ማጠቃለያ ትምህርት ሰጥተዋል።

የሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስና የመካከለኛ አመራሩን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ለአመራሩ የሚሰጠው ሁለገብ ስልጠና አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሜጄር ጄኔራል ሙላት ጀልዱ በዕውቀት የዳበረ በክህሎት የላቀና በአስተሳሰብ የበለፀገ ተተኪ ለማፍራት ያላሰለሰ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አመራሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ላይ ያለውን እውቀት በማጎልበት እንዲሁም ስልታዊ ቴክኒካዊና ታክቲካዊ ግንዛቤውን በማሳደግ አባላቱን በእውቀት ላይ ተመስርቶ በመምራት ፈጣንና ተነቃናቂ አሃድ ፈጥሮ በተልዕኮዎቹ ሁሉ ድንገተኝነትን ለማትረፍ የሚያስችለውን አስተማማኝ አቅም ስልጠናው ፈጥሮለታል ሲሉ ጀኔራል መኮንኑ ተናግረዋል።

ሜጄር ጄኔራል ሙላት ጀልዱ ሠራዊቱን በማያቋርጥ ስልጠና መገንባት የሞራል ተነሳሽነቱን ማሳደግና በጠላቶቹ ላይ የበለጠ እልህና ቁጭት ፈጥሮ ወኔና ጀግንነትን በመላበስ ስምሪቶቹን በመረጃ ላይ ተደግፎና አዳዲስ ስልታዊ እንቅስቃሴዎችን ተጠቅሞ በማካሄድ በአጠረ ጊዜና ባነሰ ኪሳራ ድል የሚቀዳጅበትን አቅም ከስልጠናው አግኝቷል ብለዋል ።
የስልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የዕዙ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ጀንበሬ ማሞ በበኩላቸው የስልጠናው ዓላማ በክህሎትና በዲስፕሊን የታነፀ የሬጅመንት እና የሻምበል አመራር እንዲሁም ብቁ የቡድን መሳሪያ ምድብተኞችን መፍጠር መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው አመርቂ ከመሆኑም በላይ የአመራሩ ድጋፍ የታከለበት በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና መሆኑን አብራርተዋል።
ዘጋቢ ፍፁም ከተማ
ፎቶግራፍ አከለ አባተ