ተልዕኳችንን በማሳካት የኢትዮጵያን ልዕልና እና የህዝባችንን ሰላም እናረጋግጣለን ሲሉ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት ተናግረዋል።
አዛዡ ምዕራብ ዕዝ በተለያዩ ጊዜያት ፀረ-ሠላም ኃይሎች ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ለመበተን የጠነሰሱትን ሴራ በጀግንነት አምክኗል፤ አሁንም በቁርጠኝነት በማምከን ላይ ይገኛል ብለዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፤ አበቃላት ይላሉ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ወደየት እየተጓዘች እንደሆነ እያወቁ እንዲህ አብዝተው የሚጮሁት ከባንዳነት ተልዕኮ የሚያገኙት ጉርሻ በልጦባቸው መሆኑን እንረዳለን ያሉት ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት የሀገራችን ህዝቦች እውነታው የቱ ጋር እንዳለ በውል ተረድተዋል፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ አይቀሬ መሆኑን ያሳየው የህዳሴ ግድባችን ታላቅ ምስክር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የይቻላል መንፈስ ከፍታና ዳግማዊ አድዋ ስኬት ደግሞ በዋዛ የተገኘ ድል ሳይሆን ለኢትዮጵያ ልዕልና በፍቃደኝነት መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተው በተግባር ማረጋገጥ የቻሉ ውድ ጀግኖች የሠራዊት አባላትና የድላችን መሠረት እንዲሁም ፅኑ ደጀን የሆኑ አርበኛ ኢትዮጵያዊያን በመኖራቸው እንደሆነም አሥረድተዋል።
የኢትዮጵያ የትንሳኤ ጉዞ ገና በጣም ረጅም ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሰረት፤ የሀገራችን ሉዓላዊነትና የህዝባችን ሠላም የህብር ጥረት ድምር ውጤት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ዜጋ ለሠላምና ልማት መረባረብ አለበት ብለዋል።
ምዕራብ ዕዝ በርካት ድሎችን ያሰመዘገበ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አዛዡ አሁንም ተልዕኳችንን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በላቀ ጀግንነት በመወጣት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር መላው የሠራዊታችን አመራርና አባላት ይበልጥ ቀን ከሌት መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ አሥረድተዋል።
ዘገቢ ፍፁም ከተማ
ፎቶ ግራፍ አከለ አባተ