የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በላቀ ብቃትና ዝግጁነት የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገልፀዋል።
ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ በየደረጃው ካሉ የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በመምከር የግዳጅ አፈጻጸም ቀጣይ ተልዕኮዎችን በተመለከተ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ ከጥንት ጀምሮ አብሮ የዘለቀና አሁንም በላቀ መልኩ የቀጠለ መሆኑን አንስተው፤ የሰራዊቱ ጀግንነት፣ ግዳጅና ተልዕኮ የመፈፀም ብቃት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ስኬቶችን እያስመዘገበች ለቀጠለችው ኢትዮጵያ የሚመጥን ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን አንስተው፤ ክብርና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ መዝለቅ የዚህ ትውልድ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የቀደሙት አያቶች በአኩሪ የጀግንነት ገድል ከነ ሙሉ ክብሯ ያስረከቡንን ሀገር እኛም በላቀ ክብርና ሞገስ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግደታ አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለጠላት አስፈሪና ለሀገር አኩሪ የሆነ ጠንካራና ዘመናዊ ሰራዊት መገንባቱን አንስተው፤ በዚህ ረገድ የምስራቅ ዕዝ የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ለላቀ ሀገራዊ ተልእኮ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በክህደት የጠላት ተልዕኮ ለማስፈፀም ቢሞክርም በዕዙ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ ዕዝ በዚሁ የግዳጅ አፈፃፀም ጽንፈኛ ቡድኑን በመከታተል እርምጃውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ወታደራዊ እርምጃው የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ዋና አዛዡ እንዳመለከቱት፤ ከአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል ጋር በመጣመር የሚደረጉት ስምሪቶች ውጤት ማምጣታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ የክልሉ የፀጥታ ሀይል ራሱን ችሎ በመንቀሳቀስ አኩሪ ግዳጅ እየፈጸመ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የኢትዮጵያን ጠላቶች ተልእኮ በመቀበል ሀገርና ህዝብን እየወጋ መሆኑን ህዝቡ በአግባቡ በመረዳቱ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም አጋርነቱን እያሳየ ሲሆን ሰራዊቱም ተከታትሎ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምስራቅ ዕዝ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደርና የጎጃም ዞኖች በመንቀሳቀስ በጽንፈኛ ቡድኑ ላይ ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
https://dfmc.mod.gov.et/
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/fdredefense.official