ምዕራብ ዕዝ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በሚገባ አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አማረ ባህታ ተናግረዋል።
ጄኔራል መኮንኑ ይህንኑ የተናገሩት ከዕዙ ጠቅላይ መምሪያ ስታፍ መኮንኖች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።
ሠራዊቱ እንደባለፉት ጊዜያቶች ሁሉ የተሰጠውን ትልቅ ሃገራዊ ግዳጅ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየፈፀመ የሚገኝ መሆኑን ገልፀው ለተልዕኮው ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት የበለጠ ድል ማስመዝገብ የሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
አሁን ላይም የዕዙ ሠራዊት በተሰማራበት ቀጠና በሽብርተኝነት ተግባር ላይ ተሰማርተው የሃገራችን የሰላም ማነቆ እየሆኑ ያሉ አሸባሪው የሸኔ ቡድን እና ፅንፈኛው ዳግም የህዝባችን ስጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ጄኔራል መኮንኑ ተናግረዋል፡፡

ሜጄር ጄኔራል አማረ ባህታ በቀጠናው የአሸባሪውን የሸኔ ቡድን በመደምሰስ ያሳካናቸውን ድሎች አቅበን የህዝባችንን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ መስራትና ከአካባቢው የመስተዳደር አካላት ፣ የፀጥታ ሃይሎች ፣ ከሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የፕሮፌሽናል ሠራዊት ባህሪን በመላበስ ተልዕኮን በላቀ ብቃት መወጣት እንደሚገባ ያሳሰቡት አዛዡ ሜጄር ጄኔራል አማረ ባህታ በሠራዊታችን የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ጥቅምና ፍላጎት ዕውን ይሆናል፤ በተጠናከረ ዝግጁነትና በላቀ ግዳጅ አፈፃፀም የኢትዮጵያ ጥቅምና ፍላጎት ይሳካልም ሲሉ ገልፀዋል።
የዕዙ ጠቅላይ መምሪያ ስታፍ መኮንኖች ለተዋጊው ክፍል የምትሰጡትን ያልተቋረጠ የተለያዬ ድጋፍ አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል ሲሉ አሳስበዋል።
 
													 
													 
													





 
        	
        
       
        	
        
       
        	
        
       
        	
        
      