“እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን” በሚል መሪ ሃሳብ የምስራቅ ዕዝ ስታፍ የሰራዊት አመራሮች፣ ዕለቱን በውይይትና ጧፍ በማብራት ስነ-ስርዓት አስበውት ውልዋል።
የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጄር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ 6ኛ ዓመት ዝክረ ሰሜን ዕዝን ስናስብ የጀግኖች ሰማዕታትን ራዕይ በማስቀጠል ተልዕኳችን በድል መወጣት አለብን ብለዋል።
ሽብርን ህልምና ሰንቁ ያደረገው ህወሓት በእብረት እና በማን አለብኝነት ተነሳስቶ ታሪክ ይቅር የማይለውን ጥቃት በሰሜን ዕዝ ሰራዊት ላይ መፈፀሙን ጠቅሰው ዕዙ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ የጀግኖቹን አደራ ማስጠበቅ አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።

ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ መቆም መገለጫው የሆነውን እና በታሪኩ ሽንፈት የማያውቀው ስራዎታችን አገሩን በእልህ፣ በወኔና በቁጭት ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ጠላቶችን ጥቃት በመመከት ተልዕኮውን የሚወጣ ሰራዊትን ባላሰበው እና ባልገመተው በራሱ ወገን መወጋቱ ያማል ሲሉ ተናግረዋል።
የምስራቅ እዝ ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ልጃለም ምትኩ በበኩላቸው ሠራዊቱ ለሀገር ህልውና የከፈለው መስዋዕትነት በታሪክ አወንታዊ አምድላይ የሚሰፍር መሆኑን ገልጸው የዛሬውና መጭዉ ትውልድ የሰላምን ዋጋ ተረድቶ ሀገርን ለማጽናት በአንድነት መቆም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኮሎኔል ልጃለም ምትኩ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ዘላቂ ፀጥታ ከማረጋገጥ ባሻገር የህዝብን አብሮነትና ወንድማማችነት ያጠናከረ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።
በዕለቱ የፓናል ውይይት፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎች (ግጥሞች) እና የሰማዕታት መታሰቢያ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡ ዘገባዉ የምስራቅ ዕዝ ነዉ
