የቀድሞው ሰሜን ዕዝ የአሁኑ ማዕከላዊ ዕዝ ከስድስት ዓመታት በፊት ጥቅምት 24 ቀን የተፈፀመውን የሰሜን ዕዝ ጥቃትና መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በዕዙ ጠቅላይ መምሪያ ዘክሯል።
ዕለቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጀር ጀነራል ሙላት ጀልዱ “እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን ” በሚል መሪ ቃል የሰሜን ዕዝ ጥቃትንና ጀግኖች ሰማዕታትን ስንዘክር የእነሱን አደራ በመወጣት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን አንድ ካልሆን በቀር የጠላቶቻችን ሴራ ማብቂያ የለውም ያሉት ምክትል አዛዡ ከኢትዮጵያዊነት ክብር ወርዶ በጎጥ ጥላ ስር መወሸቅና በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ክህደት መጨረሻው ሞትና ውርደት እንደሆነ ገልፀዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላትም በወቅቱ ከሠራዊቱ ጋር የግፍ በትር ገፈት ቀማሽ እንደነበሩ ያወሱት ሜጀር ጀነራል ሙላት ጀልዱ ሠራዊታችን ከፌደራልና የክልል ፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም ከደጀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ሁኔታውን ቀልብሶ ጠላቶቹን በማሳፈር ሀገር ማፅናቱን ተናግረዋል።

የዕዙ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጀነራል አብድሮ ከድር በበኩላቸው ሠራዊታችን በቴክኖሎጂና በሁለንተናዊ አቅም የፈጠረው ጠንካራ ዝግጁነት የጠላትን ቅስም የሠበረ መሆኑን ገልፀው ሰሜን ዕዝን ስናስብ በሁሉም ነገር ወትሮ ዝግጁነታችንን አጠናክረን ለማንኛውም ተልዕኮ ዝግጁ በመሆንም ነው ብለዋል።
በዕለቱ በዕዙ ከፍተኛ መኮንኖች የተመራ የፖናል ውይይት የተደረገ ሲሆን የህገ ወጡን ህወሃት አፀያፊ ተግባራት የሚያወግዙና አንድነትን የሚያጠናክሩ ገዥ ሃሳቦች ከመድረኩና ከታዳሚያን ቀርበዋል።
