የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈፀመው የሰሜን ዕዝ ጥቃት ስድስተኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከልና በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቧል።

በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሰራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች፣ ታሪክ ይቅር የማይለውን ጥቅምት 24 እንዳይደገም ሁሌም እንዘክራለን” በሚል መሪ ቃል ቀኑን በሻማ ማብራትና በተለያዩ የዝክረ ሰማዕታት መርሐ ግብሮች አስበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የማዕከሉ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ፣ ወግና ባህሏን ጠብቃ እንድትቀጥል ያስቻላት የአባቶች መስዋዕትነት መሆኑን ገልጸው፣ የአባቶቻችን ልጆች እንደመሆናችንም በሰራዊቱ ላይ ያልተጠበቀ ተደጋጋሚ ጥቃት ቢፈጸምብንም ጥቃቱን በመመከት ሀገርን ማዳን ችለናል ብለዋል።
የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ገዛኸኝ ፍቃዱ በበኩላቸው፣ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማዳከም ባሳዩት ፍላጎት ተባባሪ በመሆን፣ ለግል የሥልጣን ጥማት ሲል በሰራዊቱ ላይ ጥቃት የፈጸመውን የህወሀት ቡድንን በክህደት የሚያስታውስ ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ስድስተኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት አከባበር ላይ የኮሌጁ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ፣ የመከላከያ ሰራዊት ሀገረ መንግሥቱን ያጸናና ሀገርን ከመበታተን የታደገ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ የሀገርን ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የጥቅምት 24 ዝክረ ሰማዕታት ለቂምና ለበቀል ሳይሆን ያለፈው አሳዛኝ ታሪክ እንዳይደገም ለማስታወስና ከታሪኩ ትምህርት ለመውሰድ የሚታሰብ መሆኑን አመላክተዋል።
ዝክረ ሰማዕታቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት ለማስታወስ፣ የሰራዊቱን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍና እንዲህ ያለው አሳዛኝ ክስተት ዳግም እንዳይፈጠር የጋራ ኃላፊነትን ለማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ አሳይቷል።
