የመከላከያ መቻል የእጅ ኳስ ቡድን በአንጎላ በሚካሄደው 47ኛው የአፍሪካ ክለቦች የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያንና ተቋሙን ወክሎ ለመወዳደር ያደረገውን የቅድመ-ውድድር ዝግጅት ማጠናቀቁን የክለቡ ሥራ አስፈጻሚ ገልፀዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ስራ አስፈፃሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በቡድኑ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍና ወጣት ተጫዋቾችን ከሠራዊቱና ከሲቪል ማህበረሰቡ በማቀናጀት ቡድኑን ማጠናከር ተችሏል።
መቻል የአዲስ አበባ ዋንጫን በማሸነፍና በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በአህጉራዊው ውድድር የመሳተፍ ዕድል ማግኘቱንም ገልጸዋል።
በአንጎላ በሚካሄደው ውድድር የሠራዊታችንን ጥንካሬና አልሸነፍ ባይነት ለማሳየት እንሠራለን ያሉት ጀነራል መኮንኑ ኢትዮጵያንና ሠራዊቱን ወክለን ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የመቻል የእጅ ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሻለቃ ባሻ ደጀኔ ካሳይ በበኩላቸው፣ የአፍሪካ ክለቦች የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ሊግ ከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድበት ውድድር መሆኑን ጠቁመው ቡድኑ ከዚህ ቀደም በሞሮኮ በተካሄደው ውድድር በመሳተፍ ያገኘው ልምድ ለዘንድሮው ውድድር ጠቃሚ መሆኑንና ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የመቻል የእጅ ኳስ ቡድን ተጫዋቾችም በአንጎላ፣ ሞሮኮና ኡጋንዳ በተካሄዱ ውድድሮች በመሳተፍ ያገኙት አህጉራዊ ልምድ ለውድድሩ ያላቸውን ዝግጅት እንዳጠናከረ ተናግረው በውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ አብርሃም ዘርጋው
ፎቶ ግራፍ ጀረመው ጨሬ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
