በምረቃ መርሃ ግብሩ መከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ምክትል ሀላፊ ለባማና መሰረታዊ ውትድርና ስልጠና ብርጋዲየር ጀኔራል ሙሉጌታ አምባቸው ብልጫ ላመጡ ሰልጣኞች ሽልማት ካበረከቱ በኋላ መከላከያን ለማዘመንና የሠው ሃይል ፍላጎቱን ለሟሟላት የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ በስሩ ባሉት የስልጠና ተቋማት በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
መከላከያ በሁሉም መንገድ ዘመናዊነቱን እያሳደገ የመጣ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የታጠቃቸውንና የሚገለገልባቸውን መሳሪያዎች የሚጠቀም ዘመናዊና የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራትና አቅሙን ለማሳደግ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ አጠቃላይ ትምህርት መምሪያ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።
የዛሬ የመጀመርያ ደረጃ ተመራቂ መምህራን ወደ ክፍላችሁ ስትመለሱ የተማራችሁትን የማስተማር ዘዴ ከነበራችሁ እውቀት ጋር በመደመር የሰራዊቱን የአካዳሚ አቅምና የእውቀት ደረጃውን ማሳደግ ይጠበቅባችኋል ሲሉ አሳስበዋል።

የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ የአጠቃላይ ትምህርት መምሪያ ሀላፊ ኮሎኔል ተሾመ ለገሰ የስልጠና ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ሠልጣኝ መምህራኖቹ ለመምህርነት የሚያበቃቸውን የመመልመያ መስፈርት አሟልተው ከተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች የተመለመሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ሠልጣኞቹ በቆይታቸው የማስተማር ዘዴና ሌሎች የማስተማር ክህሎቶች የተማሩ መሆኑን ገልፀው ቀጣይ ወደሚመደቡበት ክፍል ሲመለሡ የሠራዊቱን የአካዳሚ አቅም የማሳደግ ሀላፊነት የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል።
