በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል አለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት “ለአለም አቀፍ ፀጥታና ደህንነት ዘላቂ አጋርነትን መገንባት” በሚል መሪ ቃል የቀጣይ አምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
በወቅቱ የመከላከያ አለምአቀፍ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ስትራቴጂካዊ እቅዱ የአፍሪካን እንዲሁም የአለምን ሰላም በጋራ ለማስከበር ሁሉም አጋሮች በአንድነት በመስራት፣ እውቀትን በመካፈል እና ኢንስቲትዩቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመደገፍ የስልጠና እና የአካዳሚክ መርሐ ግብሮቹ ለሰላም ማስከበር ጥረቶች ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን እንዲቀጥሉ ውይይቱ ጠንካራ መሠረት የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ታሪክ ከኮሪያ ጀምሮ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በሱዳን አብዬና ጁባ፣ በሶማሊያ ከፍተኛ የሆነ አለምአቀፍ ግዳጅን መፈፀሟንና እየፈፀመች መገኘቷን አንስተዋል።
በማዕከሉ የአለም አቀፍ ሰላም ማሥከበር ኢንስቲትዩት ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ገዛኸኝ ፍቃዱ ኢንስቲትዩቱ ለሰላም አስከባሪ ሃይሎች (ወታደሮች፣ ፖሊሶች እና ሲቪሎች) በግጭት ቀጠናዎች ለሚደረጉ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ዝግጁ የሚያደርግ በንድፈ ሀሳብና በተግባር በረጅምና በአጭር ስልጠና የሚሰጥበት ማዕከል መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ የአምስት አመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድም አለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁና ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች የሚፈፀሙበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በውይይቱ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ አምባሳደሮች፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ የከፍተኛ ትምርት ተቋማት ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
