መከላከያ ሠራዊት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መሰናክሎችን ተሻግሮ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚሠጠውን ተልዕኮ በጀግንነት እየፈፀመ ሠላም እና ልማትን እያረጋገጠ የሚገኝ የሀገር ክብርና መከታ ነው።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይልም የሀገር ተልዕኮ ከተሠጣቸው የመከላከያ ክፍሎች አንዱ ሲሆን የባህር ኃይል አባላት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በንጋት ሀይቅ ላይ በመንቀሳቀስ የግድቡን ደህንነት የማረጋገጥ አኩሪ ተግባር እየፈፀሙ ይገኛሉ።
አባላቱ ተልዕኳቸውን ከሌሎች የሠራዊታችን ክፍሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር መረጃ በመለዋወጥና በመናበብ ውጤታማ ስራዎችን እየሰሩ ሥለመሆናቸው ይናገራሉ።
የባህር ኃይል አባላቱ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከሚፈፅሙት የዕለት ተዕለት የግዳጅ ክትትል ባሻገር የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ለውጤት የሚያበቃቸውን ሥልጠና ጨምሮ ዝግጁነትን በሁሉም መስክ የማረጋገጥ ሥራ ይተገብራሉ። ይህ ራስን ቀድሞ የማብቃት የዝግጁነት ሥራ የሀገራችንን ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ ከግምት ያስገባና ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያበቃ አቅምና ችሎታ መላበስ የሚያስችል ስለመሆኑ አባላቱ ገልፀዋል።
በየጊዜው በሚያደርጓቸው የምድር ላይ ቅኝቶች እና ዝግጁነት የማረጋገጥ ተግባራት ሊቃጡ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችንና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።
