የመከላከያ መገናኛና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ በሥራ አፈፃፀምና በፈጠራ ሥራ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አባላት እውቅና ሰጥቷል። ለረጅም ዓመታት በታማኝነትና በትጋት ሀገራቸውን አገልግለው በጡረታ የተሰናበቱትንም በክብር ሸኝቷል።
በእውቅና እና በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የመከላከያ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት፣ በሥራ አፈጻጸም፣ በፈጠራ አስተሳሰብና በሙያዊ ብቃት ልዩ ውጤት ያስመዘገቡ አባላት ሊበረታቱና ሊደገፉ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይም በፈጠራ ሥራዎችና በቴክኖሎጂ መፍትሔዎች የተቋሙን የሥራ ቅልጥፍና ከማሳደጋቸው በተጨማሪ ወጪን መቀነስ የቻሉ አባላት ለሌሎች አርዓያ መሆናቸውን አስረድተዋል። እንዲህ ያሉ አባላትን በእውቅናና በድጋፍ ማበረታታት የግለሰቦችን ተነሳሽነት ከማጠናከር ባለፈ፣ በተቋሙ ውስጥ የፈጠራ ባህልን፣ የቡድን ሥራንና ውጤት ተኮር አሠራርን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት ለረጅም ዓመታት የሠራዊቱን ተልዕኮና የተቋሙን ዓላማ በታማኝነት፣ በዲሲፕሊንና በትጋት ያገለገሉ አባላት ያበረከቱት አስተዋፅኦ በአገልግሎት ዘመናቸው ብዛት ብቻ የሚለካ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ውስጥ ያሳዩት ጽናትና ያስመዘገቡት የጋራ ስኬት ለተቋሙ ትልቅ አስተዋፅኦ መሆኑን ገልጸዋል።
የእውቅናና የሽኝት መርሐ ግብሩ የፈጠራ ሥራን፣ ውጤታማነትን፣ የሙያ ብቃትንና ታማኝ አገልግሎትን በአንድ ላይ ያከበረ ሲሆን፣ ለተቋሙ ቀጣይ ዕድገትና የዲጂታል ሽግግር ግቦች መሳካት የሁሉም አባላት ተሳትፎ፣ ቁርጠኝነትና የፈጠራ አቅም ወሳኝ መሆኑን አሳይቷል።
