በ1943 ዓ.ም በኮሪያ ልሳነ ምድር የሰላም ማስከበር ተልዕኮን የጀመረችው ሃገራችን ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
አሁን ላይ ሃገራችን በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ እየተሳተፈች እንዳለች የገለፁት የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጄር ጄነራል አዳምነህ መንግስቴ፣ የጎረቤት ሃገራት ሰላም ለሃገራችን ሰላም ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ታምኖበት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችና አለመረጋጋቶች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የመተሳሰር እድል ስለሚኖራቸው ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ሽብርተኝነትንና የጽንፈኝነት አደጋዎችን ለመግታት የምታደርገው ስኬታማ ተግባራት ለቀጠናው ሰላም ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል፡፡
ጄነራል መኮንኑ ሀገራችንን ከስደተኞች ጫና፣ ከሽብርተኝነት ስጋት፣ ከሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ከቀጠናዊ ቀውሶች የምትጠበቀው በአጎራባች አገራት ውስጥ የሚደረገው የሰላም ማስከበር ግዳጅ ሲሳካ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተልዕኮው ፋይዳም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ግዳጁን በብቃት መወጣት እንዲችል የቅድመ-ስምሪት ስልጠናዎች በማዕከሉ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ያብራሩት ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ፤ ለኮንቲንጀንትና ለተናጠል ስምሪት መኮንኖች ስልጠናዎችን የሚያዘጋጁት ሁለት የማሰልጠኛ ማዕከላት ሠራዊቱ ተልዕኮውን በስኬት እንዲወጣ የሚጠበቅባቸውን ሚና እያበረከቱ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
ሠራዊታችን በውጭ ሃገራት በሚሰማራበት ወቅት የሰላም አምባሳደር በመሆን የኢትዮጵያን መልካም ገጽታና ወታደራዊ ስነ-ምግባር በተግባር የሚያሳይ፣ ብቃቱንና ታማኝነቱን ያስመሰከረ ኃይልም ነው ብለዋል።
