ኢትዮጵያ በወታደራዊ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ እውነታን ለዓለም በማስገንዘብ ረገድ የላቀ ስኬት ማስመዝገቧን የመከላከያ ሚኒስቴር የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ አስታወቁ። ሀገሪቱ በዘርፉ ባስመዘገበቻቸው በእነዚሁ አበይት ድሎች በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ቀጣናዊ ማዕከልነትና ፅናት ያለው ዘመናዊ ሠራዊት መገንባቷን በተግባር ማስመስከሯንም ገልጸዋል።
ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ይህንን ያስታወቁት አዲስ ለተሾሙት የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስና ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሎሜ በዶ የዋና ዳይሬክቶሬቱን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክተው በሰጡት ገለፃ ነው።
ሜጀር ጄኔራል ተሾመ፣ ዋና ዳይሬክቶሬቱ በወታደራዊ ዲፕሎማሲው መስክ ተጨባጭና ስልታዊ ድሎችን ማስመዝገቡን ጠቁመዋል። በተለይም ከሕወሓት ጋር ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሁኔታውን እውነተኛ ገጽታ በትክክል እንዲረዳ ለማድረግ የተከናወነው ጥረት ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከሚገኙ የውጭ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና ዲፕሎማቶች ጋር በተደረገ ጠንካራና ተከታታይ ውይይት፣ ቀደም ሲል የተሳሳተ አቋም ይዘው የነበሩ አገራት እውነታውን ተረድተው አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ መደረጉን አስረድተዋል። አገራዊና አሁናዊ እውነታን ለዓለም የማስገንዘቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድና በጋራ ልማት መርህ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ፍትሐዊ ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትክክል እንዲረዳውና እንዲቀበለው በማድረግ ረገድ የተሰራው የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት የቀረበውን ማብራሪያ ያዳመጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ፣ ዋና ዳይሬክቶሬቱ በወታደራዊ ዲፕሎማሲው መስክ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ጠንካራ ሥራዎችን ማከናወኑን አድንቀው፤ በቀጣይም የተገኙትን አገራዊ ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፍተኛ ትጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያላትን ተሰሚነትና ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የቻለችው በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ ጠንካራ የወታደራዊ አቅም በመኖሩና ይህንንም በውጤታማ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ማስደገፍ በመቻሏ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተቋሙ ያስመዘገባቸው የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ድሎች ሀገራዊ እውነታን ለዓለም ከማስገንዘብ ባሻገር የሀገርን የደህንነትና የልማት ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶች ለማስከበር ትልቅ ድጋፍ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህንን የተጎናፀፍነውን ቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነትና አስተማማኝ የመከላከል አቅም አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የሀገርን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም በጽናት ማስከበር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሎሜ በዶ በበኩላቸው፣ ዳይሬክቶሬቱ ባስመዘገባቸው የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ድሎች መደሰታቸውን ገልጸው፤ በዘርፉ በሕግና በአሰራር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ በመፍታት ስኬታማ ጉዞውን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉና በቅርበት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። ዘገባው መከላከያ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ነው።
