የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ልማት እና በሰው ኃይል ግንባታ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም እና የዩኒቨርሲቲውን የምርምርና የዕውቀት አቅም በማስተሳሰር፣ ለሀገራችን የመከላከያ አቅም ግንባታ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ማበርከትን ዓላማው ያደረገ ነው። ሁለቱ ተቋማት በጋራ የምርምርና ልማት ፕሮጀክቶች፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ኢንዱስትሪው ላይ ጥናቶችን ማካሄድ፣ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተግባር ልምምድ ዕድል በመፍጠር፣ የጋራ ሥልጠና ማጎልበት ፣ቤተ-ሙከራዎችንና ወርክሾፖችን በጋራ መጠቀምን ስምምነቱ አካቷል።
የመግባቢያ ሰነዱን የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕን በመወከል የግሩፑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሀብት አስተዳደር ኃላፊ ብርጋዲየር ጀነራል ዮሐንስ ቲኬሳ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርጋዲየር ጀነራል ከበደ ረጋሳ ተፈራርመዋል።
የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ምክትል ሥራ አሥፈፃሚና የሀብት አስተዳደር ኃላፊ ብርጋዲየር ጀነራል ዮሐንስ ቲኬሳ ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሀገራችንን የመከላከያ ፍላጎት በሀገር ውስጥ አቅም ለማሟላት ጠንክሮ እየሠራ መገኘቱን አውስተው፤ ስምምነት በዩኒቨርሲቲው የሚመነጨውን ዕውቀትና የምርምር ውጤት በኢንዱስትሪዎች ወደ ተጨባጭ ምርት ለመቀየር የሚያስችል ድልድይ እንደሆነ ገልፀዋል።
ብርጋዲየር ጀነራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሠራዊት ለመገንባት የሚያስፈልገውን ባለሙያ በማፍራትና ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ መገኘቱን ገልፀው ይህ ስምምነት ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ከኢንዱስትሪው ጋር በቅርበት እንዲሠሩ፣ ምርምሮች የኢንዱስትሪውን ትክክለኛ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያፈራቸው ምሩቃንም በተግባር የተፈተኑና ለኢንዱስትሪው ዝግጁ እንዲሆኑ ስምምነቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ሁለቱ ተቋማት የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም፣ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ ዝርዝር ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል።
