በተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ጁንሁይ ው በምዕራብ ኢኳቶሪያ ግዛት ደቡባዊ ሴክተር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራውን የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ጎብኝተዋል።
ሰላም አስከባሪ ሻለቃው ፈታኝ በሆኑ ቀጠናዎች ሁሉ በመንቀሳቀስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደቡብ ሱዳን ተልዕኮ የሚሰጠውን ወታደራዊ ግዳጅ በቁርጠኝነት እየተወጣ በመሆኑ በሁለንተናዊ አፈፃፀሙ እተማመናለሁ ብለዋል።
ሻለቃው እየፈፀመ ያለው ግዳጅ በቀላል የሚታይ እንዳልሆነ የገለፁት ጀነራል መኮንኑ ፤ ለበለጠ ድል እና ለደቡብ ሱዳን ሰላም ተልዕኮ ስኬት የአካባቢውን ፀጥታ ሁኔታ በመከታተል ወታደራዊ ዝግጁነትን በየጊዜው ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለማህበረሰቡ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይ በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ሜጀር ጀነራል ጁንሁይ ው ገልፀዋል።
የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ አዛዥ ኮሎኔል ምሳው ደሳለኝ በበኩላቸው ፤ ሰራዊቱ የሚገጥሙትን መሰናክሎች ሁሉ በጀግንነት እየተሻገረ የዩናሚስን ተልዕኮ ለማሳካት በላቀ ቁርጠኝነት ግዳጁን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀው ፤ የሚሰጥን ማንኛውም ተልዕኮ በፅናት ለመወጣት ሰላም አስከባሪ ሻለቃው ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
