የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ እና የሜጀር ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ የቴክኒክ ሙያተኞችን እና መሪዎችን በማፍራት ረገድ አይተኬ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀኔራል ይመር መኮነን ገለፁ። ተቋማቱ ማንኛውንም ግዳጅ በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል ዘመናዊ ሠራዊት በመገንባት ላይ እንደሚገኙም ኃላፊው አስታውቀዋል።
ጀኔራል ይመር መኮነን በሁለቱም የስልጠና ተቋማት ከሚገኙ ከፍተኛ እና መስመራዊ መኮንኖች ጋር ውይይት አዶርገዋል። በዚሁ መድረክ ላይ የሁለቱም የትምህርት ተቋማት ወቅታዊ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ታሪክና ቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው፤ በታሪክ አጋጣሚ የሌሎችን ሀገር ሉዓላዊነት ሳትደፍር፣ የራሷን ሉዓላዊነትም አሳልፋ የማትሰጥ የጀግኖች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል። የመጡባትን ጠላቶቿን በኢትዮጵያውያን አንድነት፣ በጥንካሬ እና በሠራዊቱ የጦር ጥበብ በድል አድራጊነት መንፈስ አሳፍራ መመለስ የቻለች ሀገር መሆኗንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ባሳለፈችው የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ለአፍሪካ ነፃነት ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ ማበርከቷንና በአሁኑ ወቅትም በአለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነቷ እያደገ መምጣቱን ጀኔራል ይመር አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሠራዊቱ “ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር” በሚለው የላቀ እሴት ተኮትኩቶ፣ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ግዳጅን በስኬት ለመወጣት የሚያስችል በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቅና በቴክኖሎጂ የተሟላ አቅም መገንባቱን አስረድተዋል።
ጀኔራል ይመር መኮነን በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ በተለይም የትምህርትና ስልጠና የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
