የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የፀረ-ሙስና ቀን “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ!” በሚል መሪ ቃል በውይይት፣ በኦንላይን የሀብት ምዝገባ እና በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ከፍተኛ የመንግሥትና የሠራዊት አመራሮች በተገኙበት አክብሯል።
በመድረኩ ላይ በተቋም ደረጃ የተዘጋጀውን የመወያያ ሰነድ መነሻ በማድረግ “ሥነ-ምግባር የተላበሰ አገልግሎት አሰጣጥና የፀረ-ሙስና ትግል በሎጂስቲክስ” በሚል ርዕስ ገለጻ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በቀረበው የመወያያ ጽሑፍና በተነሱ ሐሳቦች ላይ ተመሥርተው መልዕክት ያስተላለፉት የዕለቱ የክብር እንግዳ የመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ሥራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ የተጀመረውን የመከላከያ ሪፎርም ለማስቀጠል ከጥቅም ትስስር የፀዳ አሠራርን በታማኝነትና በግልጽነት ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል በሰጡት የማጠቃለያ አቅጣጫ፣ ሙስና ባሕሪውን እየቀያየረ እንደሚያጠቃ ቫይረስ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያላሽቅ፣ የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር እና የተቋምን ሞራልና መተማመን የሚያደቅ በመሆኑ በመንግሥት ደረጃ በቀይ መስመር መለየቱን ገልጸዋል።
ሠራዊታችን የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ ዋናዎቹ የሎጂስቲክስ አሠራሮች ሥነ-ምግባርን የተላበሱና ከምንም ዓይነት ስውር ትስስር የፀዱ መሆን እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠላትን አጥንተን፣ ኃይል መድበንና የስበት ማዕከሉን መትተን እንደምንደመስሰው ሁሉ፤ የሙስናና የብልሹ አሠራር ሥውር ትስስሮችንም ነቅሰን በማውጣት፣ የተጋላጭነት ቀዳዳዎችን አስቀድመን በመዝጋትና በመበጣጠስ ለሀገራችን ሉዓላዊነትና ለሠራዊታችን ክብር ያለንን ታማኝነት በተግባር ማረጋገጥ ይኖርብናል ያሉት ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን፣ ከስውር ትስስር የፀዳ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ለሠራዊቱ ሁለንተናዊ ዝግጁነትና ድል ዋስትና መሆኑን አረጋግጠዋል።
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፣ የዘንድሮው መሪ ቃል ዓለም ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መመረጡን አውስተው፤ ሙስና የጥቅም ግጭትን ከማስከተሉም ባለፈ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማጥፋት የሀገር ዕድገት ማነቆ በመሆኑ በጋራ ልንታገለው ይገባል ብለዋል።
በዕለቱም ግልጽነትና ተጠያቂነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል የኦንላይን የሀብት ምዝገባ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ የቀረበውን የመወያያ ገለጻ መሠረት ያደረገ የጥያቄና መልስ ውድድርም ተካሂዷል።
