በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት (IPSTI) በእንግሊዝ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍና በፈረንሳይ መንግሥት በጅቡቲ ከሚገኘው የፈረንሳይ የጦር ሰፈር በመጡ መምህራን የፈንጂ አደጋ ግንዛቤ ማስጨበጫ የአሰልጣኞች ሥልጠና (Training of Trainers on Explosive Hazard Awareness Training – Tot EHAT) በይፋ ተከፈተ።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የፈረንሳይ መከላከያ አታሼ ኮሎኔል ዳሚየን ሳይፕሪ፣ ሰላምና ደህንነትን በጋራ ለማስፈን ዓለም አቀፍ አጋርነትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የሰላም ማስከበር ሠራዊቱ በተለያዩ ፈንጂዎች ለሚፈጠሩ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ የሥራ አካባቢዎች ስለሚሰማሩ፣ ይህ ሥልጠና የደህንነትና የተልዕኮ አፈጻጸም ብቃታቸውን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የእንግሊዝ መከላከያ አታሼ ሌተናል ኮሎኔል ጋሪ ዎልፌንደን፣ የፈንጂ አደጋዎች በሰላም አስከባሪዎችና በሚጠብቋቸው ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደሚደቅኑ ገልጸው፣ ተሳታፊዎች በሥልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በተግባር በመተግበር የሠራዊቱን የደህንነትና የተልዕኮ ዝግጁነት እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል። የፈረንሳይ መምህራን ለሚያካፍሉት ዓለም አቀፍ ልምድና ዕውቀትም ምስጋና አቅርበዋል።
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ትምህርትና ሥልጠና ዲን ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን ወረታው፣ ሥልጠናው ሊከሰቱ የሚችሉ የፈንጂ አደጋዎችን በመለየት፣ አደጋዎችን ለመቀነስና በደህንነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ወሳኝ ዕውቀትና ክህሎት ለሠራዊቱ እንደሚያጎናጽፍ ገልጸዋል።
ሰልጣኞች የአሰልጣኞችን አቅም በማጎልበት የሚገኘው ዕውቀት በየሠራዊት ክፍሉ ከመሰማራታቸው በፊት ለወታደሮች እንዲደርስ የሚያስችል ዘላቂ የአቅም ግንባታ ውጤት እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
