በመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሁለት ሳምንታት ሲሰጥ የቆየው የስርዓተ ፆታ ማማከር (UN MGA) ስልጠና ተጠናቋል።
ከሰራዊቱ ክፍሎች ለተውጣጡ አባላት በፈረንሳይ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠው ይህ ስልጠና፣ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የስርዓተ ፆታ ጥበቃንና ሙያዊ ምክር አሰጣጥን ለማጠናከር ያለመ ነው ፡፡
በሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ገዛኸኝ ፍቃዱ የስልጠና ማጠቃለያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ለሰልጣኞቹ የተማራችሁትን ወደተግባር መቀየር አለባችሁ ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በግጭት ወቅት ሴቶች፣ ወንዶች፣ ህፃናት እና አረጋውያን ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሰራዊቱ ለህዝብ ደህንነት እና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ ስለሆነ ይህ ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ ስልጠናው እንዲሳካ የፈረንሳይ መንግስት ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በስልጠናው የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፈረንሳይ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ዳይሚ ሳይፕሪ በበኩላቸው ስልጠናው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ለሚሰማሩ የሰራዊት አባላት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል ።
በተለይም የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፆታዊ ጥቃት ሲያጋጥም ተጎጂዎች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ለማገዝ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር አመላክተው፣ በስልጠናው ዝግጅት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
