ዋና መምሪያው በጌጃ ለስትራቴጂክ መሣሪያዎች ኮር ክፍለ ጦር፣ በወለንጪቲ ደግሞ ለኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለ ጦር ያስገነባቸውን ካምፖች ነው በዛሬው ዕለት ያስመረቀው።
በዚሁ ወቅት የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ደስታ አብቼ የዋና መምሪያው ተልዕኮ የውጊያ ድጋፍና የውጊያ አገልግሎትን በብቃት መፈጸም እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ዋና መምሪያው የሠራዊቱን ኑሮ የሚያሻሽሉ የመኖሪያ ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ቢሮዎችን፣ ማሠልጠኛ ማዕከላትን፣ የመንገድና የውኃ ቁፋሮ መሠረተ ልማቶችን በመሥራት እንዲሁም የሠራዊቱን የውጊያ ግለትና ፈጣን ተንቀሳቃሽነት በመደገፍ፣ ግዳጁን በብቃት መፈጸም የሚችል የሰው ኃይል ግንባታን በጥራት እንደሚያከናውን አብራርተዋል።
የሠራዊት ካምፕ መገንባት ለዋና መምሪያው ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ እንደሆነ የተናገሩት ጄኔራል ደስታ አብቼ፣ በዛሬው ዕለትም የወለንጪቲ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለ ጦር ካምፕ እና የጌጃ ስትራቴጂክ መሣሪያዎች ኮር ክፍለ ጦር ካምፖችን በጥራትና በብቃት ገንብቶ በማጠናቀቅ ለምረቃ ማብቃቱን ተናግረዋል።
በወለንጪቲ የተገነባው ክፍለ ጦር ካምፕ በ22 ሄክታር መሬት ላይ፣ በጌጃ የተገነባው ደግሞ በ53 ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ መሆናቸውን ጄኔራል ደስታ አብቼ ጠቁመዋል። ሁለቱም የክፍለ ጦር ካምፖች የሠራዊት መኖሪያ፣ ቢሮዎችን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ የመዝናኛ ክበብ፣ የሠራዊት መመገቢያ ከነማብሰያው፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችንና ሌሎችንም አስፈላጊ መገልገያ ሕንፃዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የስትራቴጂክ ኮር ክፍለ ጦር ካምፕ የተገነባው በሜሮብ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን፣ የዲዛይንና ቁጥጥር ሥራው ደግሞ በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ተከናውኗል።
