የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን 16ኛ ዙር መደበኛ ኮርስ ተማሪዎችን በማስተርስና በመጀመሪያ ዲግሪ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የሠራዊቱ ግንባታ በሰው ኃይል ጥራት፣ በሙያዊ ክህሎት፣ በአመራር ብቃትና በቴክኖሎጂ አቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልፀው ፣የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅምን እና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ በሙያዊ ብቃት፣ በዘመናዊ አመራርና በቴክኖሎጂ የበቃ ሠራዊት እየተገነባ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በታሪኳ የውጫዊ ጫና ፈተናዎችን ያሳለፈችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም ሉዓላዊነቷንና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በቂ ዝግጁነት ያለው ጠንካራ ሠራዊት እየገነባች መሆኗን ጠቁመው ፣ የሠራዊቱ ግንባታ በቁጥር ሳይሆን በጥራት፣ በብቃትና በዘመናዊ የውጊያ አቅም ላይ መመስረቱንም አንስተዋል።

የአሁኑና የወደፊቱ የጦርነት አካሄድ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እውቀትና የመረጃ አጠቃቀም ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የሠራዊቱ አመራሮች ዲጂታል ቴክኖሎጂን፣ የጂፒኤስ ሥርዓትን፣ የኮምፒውተር አጠቃቀምንና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በብቃት መጠቀም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በተለይም የአመራር ኃላፊነት የሚሸከሙ መኮንኖች መረጃን በትክክል መተንተን፣ ቴክኖሎጂን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ማዋልና ከዘመኑ የወታደራዊ አሠራር ለውጥ ጋር መራመድ እንደሚኖርባቸውም አንስተዋል።
የአዛዥነትና ስታፍ ኮሌጁ የሚያከናውነው ሥልጠና ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ ኮሌጁ የሥልጠና ካሪኩለሙን በማዘመን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጠናከርና የሥልጠና አቅሙን በማሳደግ ለቀጣዩ የወታደራዊ አሠራር ለውጥ የበቁ አመራሮችን ማፍራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኮሌጁ ከኢትዮጵያ ባሻገር ከተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት የሚመጡ መኮንኖችን የሚያሰለጥን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል እንዲሆን የማሳደግ ራዕዩን ለማሳካት የስልጠና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የአካዳሚያዊ ብቃትን በማጠናከርና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማሳደግ ላይ እየሰራም እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ተመራቂ መኮንኖችም በኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ልምድ በተግባር በማዋል፣ ራሳቸውን በቀጣይነት በማብቃትና ከዘመኑ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር በመራመድ ለሠራዊቱ ዝግጁነትና ለሀገር ደኅንነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
