በመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል የዓለማቀፍ ሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ የፈረንሳይ መንግስት ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ በጋራ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
“በዓለም አቀፍ ሥርዓት ለውጥ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ የምትጫወተውን የሠላም ማስከበር ሚና ለማስቀጠል የሚረዱ ስትራተጂዎችና የብዙ ወገን ትብብር መዳከም የሚያስከትላቸው ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ አንገብጋቢና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን የገለፁት የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱረህማን እስማኤል ላዘጋጆቹ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከኮሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር መድረክ የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ ያላት መሆኑን የገለፁት ጄነራል መኮንኑ ይህ አኩሪ ታሪክ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍና አህጉራዊ የጋራ ሠላምና ደህንነት ዘርፍ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
በከባድና ፈታኝ የሠላም ማስከበር ግዳጅ ሠራዊታችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በመልካም ሥነ-ምግባር መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ሚና እንዲኖራት ማስቻሉን የገለፁት ሌተናል ጄነራል አብዱረህማን ባለፈው አኩሪ ታሪካችን ተማምነን ቁጭ ማለት ሳይሆን አሁን ያለውን የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ በጥንቃቄ በመገምገም ኢትዮጵያ ወደፊት በሠላም ማስከበር ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባትም ተናግረዋል።
የተዘጋጀው የምክክር መድረክ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የሠላም ማስከበር አስተዋፅኦ ለመገምገም የዓለማቀፍና አህጉራዊ ለውጦችን ተፅዕኖ ለመመርመር የፋይናንስና የአጋርነት ፈተናዎችን ለመወያየትና ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ያላትን ዝግጁነትና የወደፊት ስትራተጂዎችን ለመገምገም እንደሚጠቅምም ሌተናል ጄኔራል አብዱረህማን እስማኤል ገልፀዋል።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ የመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንቲትዩት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ገዛኸኝ ፍቃዱ ጄነራል መኮንኖችን ጨምሮ አምባሳደር ዶክተር ዮናስ አዳዬና የምክክሩ ፅሑፍ አቅራቢና አወያዮች ተገኝተዋል።
