የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወለንጭቲ መስመር የተገነባውን የልዩ ዘመቻዎች የክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ፕሮጀክት እና በጌጃ የተገነባውን የስትራቴጂክ መሣሪያዎች ኮር የአንድ ክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ መርቀዋል።
በመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ተገንብተው ለምረቃ የበቁት ሁለቱ ካምፖች ማሟላት የሚገባቸውን መሠረተ ልማቶች በሙሉ ያሟሉ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮጀክቶችን የመረቁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ዘርፍ ብቁ ለማድረግ ባከናወነው የሪፎርም ሥራ መሠረት ኢትዮጵያን የሚመጥን ሠራዊት መገንባት ተችሏል።

ተቋሙ በትኩረት እየሠራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል የሠራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ታሳቢ ያደረጉ የአኗኗር ሁኔታዎችን በዘመናዊ መልኩ መቀየር አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህም የተጀመረውን የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ሂደት ያፋጥነዋል ብለዋል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች በብዛት፣ በጥራትና በውበት ተቋሙን የሚመጥኑ ሥለመሆናቸውም አንስተዋል።
ባለፉት 7 ዓመታት የመንገድና የውኃ ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር 88 የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን የገለፁት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ አሠራሩ የተቋሙን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ጊዜና ወጪን የቆጠበ እንደነበር ገልፀዋል።
በቀጣይም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር የሚከናወኑ ተቋማዊ ፕሮጀክቶች ሌላ የግል ተቋራጭ ሳይገባባቸው በመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ራሱን ችሎ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል።
በዕለቱ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለካምፕ ግንባታዎች መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና የምስክር ወረቀትና ሽልማት አበርክተዋል።
