የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርና የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ የሠራዊቱን የጤና አገልግሎትና አስተዳደር በቴክኖሎጂ ለማዘመን በጋራ ለመሥራት በሚያሥችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተስማምተዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፦ ሠራዊቱ ተልዕኮውን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ ዘመናዊና ውጤታማ የጤና አገልግሎትና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት መኖሩ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። የመከላከያ የጤና አገልግሎትን በቴክኖሎጂና በዘመናዊ አሠራር ለማጠናከር የቴክኒክ፣ የመሠረተ ልማትና የሙያ ድጋፎች እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ሥርዓቱን ከመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ጋር በቅንጅት ለመተግበር አስፈላጊው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፣ የሀገር ፅናትና ኩራት የሆነውን ሠራዊት በጤና ዘርፍ ለማገዝ የቁሳቁስና የሙያ ድጋፎች እንደሚጠናከሩም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የተገኙት የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ የበሽታ መከላከል መምሪያ ኃላፊ ብርጋዲየር ጀነራል ሸዋዬ ሃይሌ፣ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም የቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም ያሉትን ክፍተቶችና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የትብብር መስኮች ለመለየትና የትግበራ አቅጣጫዎችን ለመቅረጽ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የሁለቱ ተቋማት የቴክኖሎጂ ትብብር የሰራዊቱን የጤና አገልግሎት ጥራት፣ የህክምና መረጃ አያያዝና የአስተዳደር ቅልጥፍና ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
በዝግጅቱ ላይ በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊዎችና የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ባለሙያዎች የጉብኝትና የሶፍትዌር ማሳያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
