የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በተቋም ደረጃ አስጀምረዋል።
በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የችግኝ ተከላን መርሀ-ግብር ያስጀመሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አውስተው ይህንኑ ዕቅድ ለማሳካት እንደመከላከያ 18 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል። የችግኝ ተከላው የመከላከያ ሠራዊቱ ባለባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ የሚከናወን ነው።
የመከላከያ ሠራዊቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመከላከል ተልዕኮውን የሚወጣ ከመሆኑም በላይ ችግኝ የመትከል ባህሉን ከሀገር አልፎ የሠላም ማስከበር ግዳጅ በሚወጣባቸው ሀገሮችም ጭምር ማሳካቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ያሳኩት ድንቅ ስራ መሆኑንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ገልፀዋል።
ከዚሁ መርሐ ግብር ጋር ተያይዞ የክረምት በጎ ስራ መርሃ ግብርም በይፋ መጀመሩንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልፀዋል።
ችግኝ መትከል ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋን ከማላበስ ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረውን ጥረት የሚያሳካ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የመከላከያ ግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ቶማስ ቱት ናቸው።
የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ሠራዊቱ በሚገኝባቸው ሁሉም አካባቢዎችና ከሌሎች ሚኒስቴር ተቋማት ጋር የሚተገበር ነው ብለዋል።
መከላከያ በበጎ ፈቃድ ረገድ ከዚህ ቀደም ለተቸገሩ ወገኖች ቤት በመስራት ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ደም በመለገስና ችግኝ በመትከል ያበረከተውን አስተዋፅኦ ገልፀዋል።
“ከካምፓችን ወደ ህዝባችን” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው መርኃ ግብር በዚህ የክረምት ወቅትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።
በችግኝ ተከላና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የመከላከያ ግብርና ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ቶማስ ቱት የፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ጀነራል መኮንኖች የሠራዊቱ አመራሮች የመከላከያ የክብር አባላትና የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ አብዮት ዋሚ
ፎቶግራፍ ተሠማ ኡርጌሳ





