የሠራዊታችንን ህዝባዊነት በቀላሉ መግለፅ በእጅጉ ይከብዳል። ምክንያቱም የምናወራው በግጭት መሐል በሚገኝ ፋታ እንኳን ሳይቀር የጉልበት፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ስለሚያደርገው የመከላከያ ሠራዊት ነውና።
ሠራዊታችን አስተዋይ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን የሚመለከት የህዝባችን አለኝታ ነው። ምክንያቱም ሠራዊታችን ተወግቶም እንኳን የማያኮርፍ ፣የማያቄም፣ ህዝባዊነቱን በተግባር የሚያሳይ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው ጀግና የህዝብ ልጅ ነው።
ሠራዊታችን በግጭት መሐል በተገኘች ክፍተት እንኳን አቅመ ደካሞችን ሲያይ ልቡ ያዝናል፤ ስሜቱም ይጎዳል ምክንያቱ ደግሞ እርሱም ከኢትዮጵያ ህዝብ ማህፀን የተገኘ ነውና።
በተለይም ሠራዊታችን ከተገነባባቸው ዕሴቶች አንዱ ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ነውና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ህዝብን ያስቀድማል ስለህዝብም ሲል አይተኬ የሆነችውን አንድያ ነብሱን አሳልፎ ይሰጣል።
አንዳንዶች ሠራዊታችንን በግርምት ይመለከቱታል ተሰድቦ፣ ተወግቶ፣ ግፍና በደል ደርሶበት እንኳን በደሉን ረስቶና ትቶ ህብረተሰቡን ሲደግፍ በማየቱ በህዝባዊነቱ ጥግ ይደነቃሉ።
በርግጥ ህዝብ እንደ ህዝብ የሚጠላም የሚወገዝም አይደለም ነገር ግን ባለማወቅ የፅንፈኞቹን ዓላማ ያራመደና ከእነርሱም ጋር የተሰለፈ የለም ማለት ግን አይደለም።

ሠራዊታችን በደጀኑ ሀዝባችን ይተማመናል። ለዚህ ነው በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ለህዝባችን ሠላምና ደህንነት መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ የማይለው።
ሰሞኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ በላይ ዘለቀ ክፍለጦር ሬጅመንቶች ግዳጅና ተልዕኳቸውን በሚወጡበት ቀጣና ለሚገኙ አርሶ አደሮች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ስብላቸው እንዳይበላሽ በማሰብ ትጥቃቸው ሳይላላ ወደ አራት ሄክታር የሚገመት የጤፍ ማሳን አጭደው ለአርሶ አደሩ አስረክበዋል።
ይህ መጣብን ሳይሆን መጣልን የሚባልለት ሠራዊት ለአቅመ ደካሞቹ ያደረገው ድጋፍ በበርካታ የአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ግርምትን አጭሯል። ምክንያቱም አስተሳሰቡ ላይ በባንዳዎቹ የተዘራበት የጥላቻ ወሬና በተግባር መሬት ላይ ያለው እውነታ የተገላቢጦሽ በመሆኑ ነው።
በተለይ አናቶች መጣልን ያሉትን ሠራዊት ሲመለከቱ አዘኔታቸውን ፣ፍቅራቸውንና ናፍቆታቸውን ደረታቸውን እየደቁ በስሜት ገልፀዋል።
ይህ ዘመን የማይሽረው የሠራዊታችን ህዝባዊት በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ ዕሴት ስለመሆኑ በዚህች አጭር ፅሁፍ መግልፅ ክብደቱን ማሳነስ ስለሚሆን በሌላ ርዕሰ ጉዳይ የምንመለስበት ይሆናል።
በአጠቃላይ ግን የሠራዊታችን ህዝባዊነት ሲወሳ የማይዘነጋው የአስተማማኙ የደጀን ህዝባችን ውለታ የማይካድ ሃቅ ነውና የእነዚህን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ወርቃማ ዕሴት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባናል።
