በሶማሊያ በሠላም ማሥከበር ተልዕኮ ላይ የተሠማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ሴክተር አመራሮች የተሠጣቸውን ሠላም የማረጋገጥ ተልዕኮ በውጤት እየፈፀሙ እንደሚገኙ ተገለፀ።
በሶማሊያ የሴክተር ሶስት ዋና አዛዥ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ተክሉ ሁሪሳ የሴክተር አዛዥነት ቆይታቸውን በሚገባ አጠናቀው ኃላፊነታቸውን የ9ኛ ዙር ሴክተር ሶስት ዋና አዛዥ ሆነው ለተመደቡት ብርጋዲየር ጄኔራል ሃሺም መሃመድ አስረክበዋል፡፡

ብርጋዲየር ጄኔራል ተክሉ ሁሪሳ ላለፉት 18 ወራት ከሠላም አሥከባሪ አመራርና ከአባላት እንዲሁም ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ብሎም ከማህበረሰቡ ጋር በመግባባት የሃገርን ጥቅም ያስቀደመና ተቋምን የሚያኮራ ግዳጅ መወጣታቸውን ገልፀው የተረከቡት አመራርና የ9ኛ ዙር ሰላም ማስከበር አባላት ይህንን አኩሪ ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባቸው ተሞክሮ አስተላልፈዋል፡፡
ብርጋዲየር ጄኔራል ሃሺም መሃመድ በበኩላቸው የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ታሪክ ያላትን ስምና ዝና እንደሚያስቀጥሉ ገልፀዋል፡፡
የሴክተር 3 አመራሮች በባይደዋ አየር ማረፊያ በመገኘት ግዳጃቸውን አጠናቀው ወደ ሃገር ቤት ለተመለሱት ብርጋዲየር ጄኔራል ተክሉ ሁሪሳ ሽኝት አድርገውላቸዋል፡፡
